ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቀን 10 ሰዓት በሚጀምር ጨዋታ የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ። ንግድ ባንኮች ከተከታታይ ውጤት አልባ ጉዞ በኋላ በሊጉ 20ኛ ሳምንት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል። በአንጻሩ ሀዋሳዎች ከኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ለማገገም ነው ዛሬ የሚጫወቱት።
ንግድ ባንክ 40 ነጥብ ሠብሥቧል። ከተከታዩ መቻል በግብ ክፍያ ተሽሎም ሊጉን እየመራ ነው። ከዚህ በፊት በጠንካራ ተጋጣሚነቱ የሚታወቀው ሀዋሳ ግን ዘንድሮ በልኩ አይገኝም። በእስካሁን የሊጉ ጉዞ የሠበሠበው 26 ነጥብም 10ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል። ቡድኑ በምርጥ ብቃት በሚገኘው ዓሊ ሱሌማን እያታገዘ ግቦችን ቢያስቆጥርም በሌላው የሜዳው ክፍል በሚቆጠሩበት ግቦች ጉዞውን ወጥ እንዳይኾን አድርጎታል።
ምሽት አንድ ሰዓት ደግሞ ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ ይገናኛሉ። ሁለቱ ቡድኖች አሁናዊ ብቃታቸው ለየቅል የሚወራ ነው። ድሬዳዋዎች አሠልጣኝ መቀየራቸውን እና ሊጉ ወደ ከተማቸው መሄዱ ምክንያት በሚያስመስል መልኩ የተሻለ መነቃቃት ላይ ይገኛሉ። በ29 ነጥብ የሊጉ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ወላይታ ድቻ የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል። የስድስት ጨዋታዎች የድል አልባ ጉዞ ውስጥ ነው። በአራቱ ሲሸነፍ፣ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል። በደረጃ ሰንጠረዡ በ24 ነጥብ 12ተኛ ላይ መቀመጡን የሶከር መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!