“ለኢኳቶሪያል ጊኒ እግር ኳስ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እናደርጋለን” ካፍ

0
294

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ (ዶ.ር ) ኢኳቶሪያል ጊኒ በእግር ኳስ ዙሪያ እያደረገች ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ ከሰሞኑ ጎብኝተዋል። በተለይም ሀገሪቱ ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በአካዳሚ አሠባሥባ ለማሥልጠን እያደረገች ያለውን ጅምር ሥራ አወድሰዋል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎ በበኩላቸው ሀገራቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚገጠሙላቸው የእግር ኳስ አካዳሚዎችን ለመገንባት የቦታ መረጣ መደረጉን ጠቁመዋል።
ይህ ዕቅዳቸውም እውን እንዲኾን ካፍ የቁሳቁስ እና የባለሙያ ድጋፍ እንዲኹም እገዛ እንዲያደርግላቸው ነው የጠየቁት።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ (ዶ.ር ) ኢኳቶሪያል ጊኒ በእግር ኳስ ዙሪያ እያደረገች ያለውን ልማታዊ ሥራ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚኾን በማለት አድንቀዋል።
ሀገሪቱ ታዳጊዎችን በአካዳሚ እያስተማረች ለማሠልጠን እያደረገች ላለው እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሞቴሴፔ ሳኦ ቶሚ እና ፕሪንሲፔ ጊኒ ቢሳውን በመጎብኘት ከተለያዩ የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል። ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ሞሮኮን እየጎበኙ እንደኾነም ካፍ ኦን ላይን ኒውስ እና ዥንዋ ዘግበዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here