” የኅያላኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጥጫ “

0
388

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይመለሳል። ለእግር ኳስ አፍቃሪያን የተሻለ መዝናናትን ያሚያሳዩ የተባሉ መርሐግብሮችም ዛሬ ይካሄዳሉ። አርሰናል ከባየርሙኒክ፣ ሪያልማድሪድ ከማንቸስተር ሲቲ ምሽት አራት ሰዓት ጀምሮ ይጫወታሉ።

አርሰናል ከ15 ዓመታት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ ምቾት ከማይሰጥ ተጋጣሚው ባየርሙኒክ ጋር ይጫወታል። አርሰናል ባየርሙኒክን በገጠመባቸው ጨዋታዎች በጥሩ የሚነገር ታሪክ የለውም። በሻምፒዮንስ ሊግ የተገናኙባቸው የቅርብ ሦስት ጨዋታዎች በባየርሙኒክ 5 ለ 1 አሸናፊነት መጠናቀቃቸውን የቢቢሲ መረጃ ያሳያል። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ በፊት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ተገናኝተው በሁሉም አጋጣሚ ባየርሙኒክ አሸንፎ ወደቀጣይ ዙር አልፏል።

ለአርሰናል መልካሙ ነገር የዘንድሮ ጥንካሬው እና የባየርሙኒክ ባልተለመደ መልክ ከቦንደስሊጋው ዋንጫ ውጭ ኾኖ መገኘት ነው። አርሰናሎች በፕሪምየር ሊጉ በተለየ ጥንካሬ እየተጓዙ ነው። ቡድኑ ብዙ ግቦችን የሚያስቆጥር እና በመከላከልም የተዋጣለት ነው። ይሄን ጥንካሬውን በጀርመኑ ክለብ ላይ ካስቀጠለ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ የተሻለ እድል ይኖረዋል።

በአንጻሩ የጀርመኑ ኅያል ክለብ ዘንድሮ በሚዛኑ አይገኝም። በላሊጋው ባየር ሊቨርኩሰን ክብሩን ሊደምቅበት የቀረው ከቀሪ ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ብቻ ነው። በጀርመን ዋንጫም ከውድድር ውጭ ኾኗል። ዓመቱን ያለዋንጫ ላለማጠናቀቅ የሙኒክ እና የሀሪ ኬን የሞት ሽረት ሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ኾኗል። ሀሪ ኬን በቶትንሀም መለያ አርሰናልን በገጠመባቸው 19 ጨዋታዎች 14 ግቦችን አስቆጥሯል።

ሪያልማድሪድ ከማንቸስተር ሲቲ ሌላኛው አጓጊ የምሽቱ መርሐግብር ነው። ሁለቱ ቡድኖች በተከታታይ ዓመታት እየተገናኙ ነው። የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሁለቱ ክለቦች በተደጋጋሚ መገናኘት ባሕል አየኾነ ነው፤ ማድሪድን በተከታታይ ማሸነፍ ከባድ ነው ሲል ሃሳቡንም ሰጥቷል።
ሲቲ ባለፈው ዓመት ማድሪድን 5 ለ 1 በኾነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሱ ይታወሳል። ከዚያ በፊት ደግሞ አሸናፊነቱ የስፔኑ ክለብ ነበር። ማድሪዶች ዘንድሮ በላሊጋው ወጥ በኾነ አቋም መሪ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሲቲዎችም ከአርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር ለፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ አንገት ለአንገት ተናንቀዋል።

ካርሎ አንቾሎቲ ሲቲን ለማሸነፍ የተለየ የሥነ ልቦና ጥንካሬ ያስፈልገናል የሚል ሃሳብ አንስተዋል። በሁለቱ ቡድኖች በኩል ጨዋታን ማሸነፍ የሚችሉ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ብዙ ናቸው። ቢቢሲ በቀዳሚነት ያነሳቸው ግን ከማድሪድ በኩል ጅዲ ቢሊንግሃም እና ቪኒሲየስ ጁኔርን፣ በሲቲ በኩል ደግሞ ኬቨን ዲብሮይናን እና ፊል ፎደንን ነው። አጥቂው ኸርሊንግ ሀላንድ ባለፈው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ውጤታማ ባይኾንም በዚህ ጨዋታ ከሚጠበቁት ውስጥ ነው። የኅያላኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጥጫ ክፍል አንድ ምሽት አራት ሰዓት ይጀምራል። ከፍል ሁለት የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ ከሳምንት በኋላ ይጠበቃሉ።

ዘጋቢ: አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here