በሩጫ አንቱ የተሰኘችው ሀገር በእግር ኳሱ ለምን!?

0
286

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ1960 በፋሽስት ሀገር ጣሊያን ሮም ከተማ በባዶ እግሩ ማራቶንን ሩጦ የኢትዮጵያን ስም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አስጠርቷል፤ የዓለም ሕዝብም “ኢትዮጵያ! ጣልያንን ሁለት ጊዜ አሸነፈች፤ አንድም በጦርነት ሁለትም በስፖርት” አስብሎ አሳልቆባታል፤ ሻምበል አበበ ቢቂላ።

የዚህን እንቁ አትሌት የአሸናፊነት ሥነ ልቦና(ወኔ) በርካቶች ተላብሰውም ለዓመታት ኢትዮጵያ እና ሩጫ አንዱ የአንዱ መለያ እስከመኾን ደርሰዋል። በወንዶች እነ ምሩጽ ይፍጠር፣ በላይነህ ዴንሳሞ፣ ማሞ ወልዴ፣ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፤ በሴቶች ደራርቱ፣ ጌጤ፣ ፋጡማ፣ ጥሩነሽ እና መሰሎች አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ በኩራት ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተለይ በወንዶች ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ውጤት እያገኘች አይደለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ አብርሃም(ዶ.ር) እንዳሉት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተዳከመውን የሀገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲያንሰራራ ፌዴሬሽኑ በስፖርቱ ውስጥ ባለፉ ሙያተኞች እንዲመራ ማደረግ ተገቢ መኾኑን ያነሳሉ።

ዶክተር አብርሃም አክለውም ክለቦች ተተኪ ወጣት አትሌቶችን በቁጥርም በጥራትም አብዝተው ማፍራት ኹነኛው መፍትሔ እንደኾነ እና በዚህ ዙሪያ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። ፌዴሬሽኑም እንደተባለው በአዲስ ከማዋቀር ባለፈ መሪዎች በዓለም አቀፍ ሩጫ ክብር እና ዝና ያተረፉ ኾኑ። ለአብነት ሻለቃ ኃይሌ፣ ኮማንደር ደራርቱ፣ ስለሽ እና ሌሎችም ወደ መሪነት የመጡበትን ኹኔታ ዶክተር አብርሃም በአውንታ አስታውሰዋል።

ደራርቱ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አባል እንዲሁም የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት በመኾን እያገለገለች ትገኛለች፡፡ እነ ደራርቱም አትሌቲክሱ ወደ ከፍታው እንዲመለስ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ማለትም ከትምህርት፣ ከመከላከያ፣ ከጤና፣ ከባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አሥተዳደር ኀላፊዎች ጋር መክረው እና ዘክረው መንግሥታዊ ተቋማቱ አቋርጠውት የቆዩትን ስፖርታዊ ግንኙነት በማደስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በማድረግ የአትሌቲክሱን ትንሳዔ አብስረዋል ሲሉ አብራርተዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በርካታ ሴት እና ወንድ ወጣት አትሌቶችን በክለብ በማቀፍ በባለሙያ እያሠለጠኑ ይገኛሉ ብለዋል። አትሌቶችም በቡድናቸው ከሚሰጣቸው ሥልጠና በተጨማሪ በተናጠል እና በቡድን ሥልጠናቸውን አጠናክረው ቀጠሉ።
መደበኛ እና መደበኛ ባልኾኑ ውድድሮች አቋማቸውን በመገምገም ጥሩ ጎናቸውን ይበልጥ አጠናከሩ። ድክመቶቻቸውንም ጠንክረው በመሥራት በማረም ለተሻለ ውጤት እንዲሠሩ እየተደረገ ያለውን ሁኔታ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

እነዚህ ተግባራት ውጤት እያመጡ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አብርሀም “በጋና አክራ ከተማ የተካሄደው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የተገኘው ውጤት ማለፊያ ማሳያ ነው” ብለዋል። ታዲያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው እምርታ ለምን በእግር ኳሱ ላይስ ውጤታማ መኾን ተሳነው?
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጀመረው በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ነው። በሀገሪቱም ከሚዘወተሩ የስፖርት ዓይነቶች በተወዳጅነቱ ቀዳሚ ለመኾን በቅቷል። ይሁን እንጂ ስፖርቱ ባስቆጠረው እድሜ እና በተወዳጅነቱ ልክ ወደፊት መራመድ ተስኖታል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሥራች የኾነችው ኢትዮጵያ ፊፋ በመጋቢት ወር 2024 የሀገራት ደረጃ በፊፋ ከተመዘገቡ 54 የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ 42ኛ ላይ መገኘቷ የዘርፉን የኋልዮሽ ዝግመት ያመላክታል ነው። ብሔራዊ ቡድኑ በመሰረተው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ 31 ዓመታትን መጠበቁ ሳያንስ ተመልሶ ከውድድሩ መጥፋቱ በደንብ ቆሞ ማሰብን የሚጠይቅ ነው።

ዶክተር ጋሻው አብዛ በታውሰን ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። እሳቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለምን ውጤታማ እንዳልኾነ በአንድ ወቅት በሠሩት ጥናት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቁልፍ ችግር የእግር ኳስ ልማት ላይ አለማተኮሩ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ አስነብቧል።

ዶክተር ጋሻው እንዳሉት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት ለተጨዋቾች ደመወዝ ብቻ በአማካይ 40 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ። ይህ ክፍያ ከአፍሪካ በሊግ ደረጃቸው እና አደረጃጀታቸው ከኢትዮጵያ የተሻሉ ከሚባሉት በርካታ ሀገራት በእጅጉ የላቀ ነው በማለት ገልጸውታል።

የደመወዝ ክፍያውን በንጽጽር ያስቀመጡት ዶክተር ጋሻው በኢትዮጵያ የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ከፍያ በአማካይ 2 ሺህ 667 ዶላር እንደኾነ እና በ50 ብር ምንዛሬም ሲታሰብ 133 ሺህ ብር ገደማ እንደሚደርስ አስረድተዋል። በጋና የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ክፍያ በአማካይ 1 ሺህ ዶላር ነው፤ በናይጄሪያ ደግሞ 1 ሺህ 250 ዶላር ሲኾን በኬንያ በአማካይ 800 ዶላር መኾኑን ዶክተር ጋሻው በሠሩት ጥናት አመላክተዋል።

የእነዚህ ሀገራት የእግር ኳስ ቡድኖች በታዳጊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶቻቸው አብቅተው የሚያወጧቸውን ተጫዋቾች ለትልልቅ ቡድኖች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት ባለፈ ብሔራዊ ቡድናቸው ጠንካራ እንዲኾን አድርጎታል ይላሉ። በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች በአንጻሩ በከፍተኛ ወጭ ከውጭ ተጫዋቾችን ያስፈርማሉ። ለአብነት የአብዛኞቹ ክለቦች ግብ ጠባቂዎች የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው። “እነዚህ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ደግሞ የሰው ወርቅ የሰው በመኾኑ ለብሔራዊ ቡድናችን መሰለፍ አይችሉም።

ስለዚህ ክለቦች በረጅም ጊዜ እቅድ እንደ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ጊኒ፣ ግብጽ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ አልጀሪያ፣ ሴኔጋል…ኹሉ ታዳጊዎች ላይ በመሥራት ከክለብ ባለፈ ጠንካራ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን በመፍጠር የስፖርት ቤተሰቡን የውጤት ጥማት ማርካት ይኖርባቸዋል” ብለዋል ዶክተር ጋሻው ።
ለ19 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የቆየው እና በሰርቪያ፣ ግብጽ፣ አልጄርያ እና ቤልጄየም የተጫወተው ሳልሃዲን ሰዒድም በዶክተር ጋሻው ሐሳብ ይስማማል። እግር ኳሱ ውጤታማ እንዲኾን ከላይ እስከ ታች ታዳጊዎች ላይ መሠራት አለበት ባይ ነው ሳልሃዲን።

እናም የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደ አትሌቲክሱ ኹሉ አድጎ ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተተኪዎች ላይ መሥራት ይገባል። በአትሌቲክሱ የአበበን እግር የተከተሉት ትናንትም ፣ዛሬም በውጤት እየደመቁ ታሪክ አስቀጥለዋል። በእግር ኳሱ ትናንት ከሀገራቸው አልፈው ለአፍሪካ እግር ኳስ መሰረት የጣሉት ይድነቃቸው ተሰማ፣ መንግስቱ ወርቁ እና መሰሎች ድካም እና ውለታ እንዲሁ እንዳይቀር ከልብ መሥራት ገና የሚጠበቅ ሥራ ኾኗል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here