ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ቦሪሲያ ዶርትሙንድ ፒኤስጅን፣ ኒውካስትል ደግሞ ኢሲሚላንን ይገጥማሉ። ዶርትሙንድ ጥሎ ማለፉን ቀድሞ ተቀላቅሏል። ፒስጂ፣ ኒውካስትል እና ሚላን ዛሬ በሚያስመዘግቡት ውጤት የሻምፒዮንስ ሊግ ቆይታቸውን ይወስናሉ።
በምድብ አምስት አትሌቲኮ ማድሪድ ከላዚዮ፣ ሴልቲክ ከፌየኖርድ ዛሬ ይጫዎታሉ። ጨዋታዎቹ ከመርሐ ግብር ማሟያነት ያለፈ ሚና የላቸውም። አትሌቲኮ እና ላዚዮ 16ቱን ቀድመው ተቀላቅለዋል።
በተመሳሳይ የምድብ ሰባት የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ምሽት ሲካሄዱ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ሰርቢያ ተጉዞ ሬድ ስታር ቤልግሬድን ይገጥማል። አርቢ ሊፕዚንግ ደግሞ ያንግ ቦይስን ይጋብዛል።
በመጨረሻው ምድብ ፖርቶ ከሻካታር ዶኔስክ፣ ሮያል አንቲወርፕ ከባርሴሎና ይገናኝሉ። ባርሴሎና ከዛሬው ጨዋታ በፊት የጥሎ ማለፍ ቦታውን አረጋግጧል። ፖርቶ እና ሻካታር እኩል ዘጠኝ ነጥብ ይዘው እርስ በእርስ ይገናኛሉ። የጨዋታው አሸናፊም ባርሴሎናን ተከትሎ አላፊ ይኾናል።
ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች የየምድቡ አላፊዎች ሲታወቁ ማንቸስተር ዩናይትድ ከውድድሩ ውጭ ኾኗል።ከምድቡ ባየርሙኒክን ተከትሎ ኮፐን ሃገን ኣላፊ ኾኗል። በምድብ ሁለት አርሴናል የበላይ ኾኖ ሲያጠናቅቅ የኔዘርላንዱ ፒኤስቪ አይንዶቨን ተከትሎታል።
ሪያልማድሪድ የምድብ ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በምድብ ሦስት ቀዳሚ ኾኖ አጠናቅቋል። ናፖሊም ጥሎ ማለፉን መቀላቀል ችሏል። ምድብ አራት ላይ ሪያል ሶሴዳድ እና ኢንተር ሚላን እኩል 12 ነጥብ በመያዝ አጠናቅቀዋል። በግብ ክፍያ የተሻለው ሪያል ሶሴዳድ የምድቡ ቀዳሚ ነው። ቀሪ አላፊ ቡድኖች ዛሬ ከተለዩ በኋላ 16ቱ ቡድኖች በእጣ የጥሎ ማለፍ ተጋጣሚያቸውን ይለያሉ።
ዘጋቢ፦ አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!