አዲሱ ዓመት የተመቸው አርሰናል ሩጫው በዋንጫ ይጠናቀቅ ይኾን?

0
570

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አዝናኝ እግር ኳስን በመጫዎት በመላው ዓለም ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። ነገር ግን ጨዋታን ከውጤት ጋር ማስታረቅ አለመቻሉ ያስተቸዋል። አንደ ቢቢሲ መረጃ አርሰናል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል።

በተለይ ውጤታማው አሠልጣኝ አርሰን ቪንገር ክለቡን ከተሰናበቱ በኋላ ክለቡ ከተፎካካሪነት ወርዶ ታይቷል። ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፔናዊ አርቴታ እየተመራ ክለቡ በደጋፊዎች ተስፋ የሚጣልበት እንቅስቃሴ እያሳየ ነው። በ2022/23 የውድድር ዘመን ዋንጫውን ለማግኘት ብዙ ርቀት የተጓዙት መድፈኞቹ የሚታወቁበት ወጥ ያልኾነ አቋም በመጨረሻ ባዶ እጃቸውን አስቀርቷቸዋል።

ከአምናው በተሻለ ጥንካሬ ዘንድሮ ለዋንጫው እየተፋለመ ያለው አርሰናል የአውሮፓውያኑ 2024 ከገባ ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ አልተሸነፈም። በሊጉ 10 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን ሲረታ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው ነጥብ እየተጋራው። በእነዚህ ጨዋታዎች 35 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ አራት ግቦችን ብቻ ነው ያስተናገደው። በስድስት አጋጣሚዎች ደግሞ መረቡን አላስደፈረም። እነዚህ ቁጥሮች የዘንድሮው አርሰናል ወደ መጨረሻ እየጠነከረ ለመኾኑ ማሳያ ብሎ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በፌስቡክ ገጹ ያስቀመጣቸው ናቸው።

በእነዚህ ጨዋታዎች ያስመዘገበው ነጥብ ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ የተሻለም ነው። ይህ የአርሰናል መሻሻል በውድድሩ መጨረሻ የዋንጫ ባለቤት ያደርገው ይኾን የሚለው ግን ቀጣይ የሚታይ ይኾናል። ለጊዜው ግን አርሰናል በተለያዩ ዕይታዎች እና ግምቶች የአርሰናል የዋንጫ ባለቤት ኾኖ ማጠናቀቅ 23 በመቶ ሊኾን እንደሚችል ቢቢሲ አስነብቧል። ሊቨርፑል 42 በመቶ እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ 35 በመቶ ግምት በማግኘት ከአርሰናል በላይ ተቀምጠዋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here