ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፊፋ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክን እንዲመሩ ከምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) አራት ዳኞችን መምረጡን አሳውቋል። በ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ እግር ኳስን ጨምሮ 32 የስፖርት ውድድሮች ይካሄዱበታል። ውድድሩም እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11ቀን 2024 በፈረንሳይ ፓሪስ ይካሄዳል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዞንም አራት ዳኞችን መምረጡን አስታውቋል። እነሱም ከሱዳን እስማኤል ሞሐሙድ አሊ፣ ከጅቡቲ አሕመድ ሊባን አብዱልራዛቅ፣ ከኬንያ ስቴፈን ይምቤ እና ከዩጋንዳ ሻሚራ ናባዳ (ሴት ዳኛ ናችው) የፓሪስ ኦሊምፒክን እንዲመሩ በፊፋ መመረጣቸውን የሴካፋ የዳኞች ኀላፊ አሊ አሕመድ ለካፍ ኦንላይን ኒውስ ተናግረዋል።
አሊ አሕመድ “ሴካፋ ዳኞቻችንን ለፓሪስ ኦሊምፒክ በመምረጡ በጣም ደስተኞች ነን፤ ኩራትም ይሰማናል” ብለዋል። ። በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የፊፋ እግር ኳስ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሊቦትስ ኮይ እንዳሉት ከ45 ሀገራት የተውጣጡ 89 የጨዋታ ኅላፊዎች፣ 21 ዳኞች፣ 42 ረዳት ዳኞች፣ 20 የቪዲዮ ረዳት ዳኞች መመረጣቸውን አስታውቋል። ቀሪዎችን ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ደግሞ ከሰሞኑ እናሳውቃለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!