የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ይካሄዳሉ።

0
417

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዋንጫ ባለቤትነት የሚደረገው ትንቅንቅ እየጠነከረ ነው። ቀጣይ የሚካሄዱ ጨዋታዎችም በዋንጫ የመጨረሻ መዳረሻ እና ከታች በሊጉ የመቆየት እና የመውረድ እጣን የሚወስኑ ኾነው በጉጉት ይጠበቃሉ። በሊጉ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይከናወኑበታል። ከዛሬ ጨዋታዎች መካከልም ዌስትሃም እና ቶትንሃም የሚገናኙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሊጉ ጅማሮ የተመሰገነ አቋም ያሳዩት ቶትንሃሞች አሁን ራሳቸውን የሊጉ አምስተኛ ደረጃ ላይ አግኝተውታል። በቀጣይ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመኾንም ከፊቱ ካለው አስቶን ቪላ እና ከኋላው ከሚከተለው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ይፎካከራል። ዌስትሃሞችም በአውሮፓ መድረክ የሚያሳትፋቸውን ውጤት ለማግኘት ትግል እያደረጉ ነው። ለዚህም ነው የዛሬ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተሻለ የመሸናነፍ ትግል እንደሚደረግበት የተጠበቀው።

በሌላ ጨዋታ በአምና አቋሙ የማይገኘው ኒውካስትል ከኤቨርተን ይገናኛሉ። ኤቨርተን የመውረድ ስጋት ያለበት ቡድን ነው። ከወራጅ ቡድኖች ለመራቅ በዛሬው ጨዋታ ነጥብ ማግኘትን እያለመ ነው ኒውካስትልን የሚገጥመው። በሌሎች መርሐግብሮች ኖቲንግሃም ፎረስት ከፉልሃም፣ በርንማውዝ ከክ.ፓላስ እና በርንለይ ከዎልቭስ ይጫወታሉ። ኖቲንግሃም ሌላኛው በሊጉ ለመቆየት እየጣረ ያለ ቡድን ሲኾን በርንለይ በሊጉ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው።

በዋንጫው ፉክክር ላይ እና ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ተጽዕኖ የሚኖራቸው ቀሪ ጨዋታዎች ደግሞ ነገ ይካሄዳሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ሐሙስ ይደረጋል። ፕሪምየር ሊጉን የክሎፑ ሊቨርፑል በ67 ነጥብ እየመራ ነው። አርሰናል በ65 ፣ ማንቸስተር ሲቲ በ64 ይከተላሉ። ከታች ሼፊልድ በ15 ነጥብ የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ አርፏል። በርንለይ እና ሉተንም ሌሎች የሊጉ ቀይ መስመር ላይ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው።

የፕሪምየር ሊጉን ከፍተኛ ጎል አሰቆጣሪነት ኸርሊንግ ሀላንድ በ18 ግቦች ይመራል። መሐመድ ሳላህ፣ የአስቶንቪላው ኦሌ ዋትኪንስ እና የበርንማውዙ ዶሚንክ ሶላንኬ እያንዳንዳቸው 16 ግቦችን አስቆጥረው ሁለተኛ ደረጃን እንደያዙ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here