እንጅባራ: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ስፖርት ለሰላም እና ለልማት በሚኖረው ፋይዳ ላይ ያተኮረ ውይይት በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል። በውይይቱ መነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ አማረ መብራት ስፖርት ሰላምን በማስፈን ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ወጣቱን ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማራቅ በስፖርት ቤተሰቦች መካከል ወንድማማችነትን፣አንድነት እና ትብብርን እያላላ መምጣቱንም አቶ አማረ ተናግረዋል። ውይይቱ በእንጅባራ ከተማ እና አከባቢው ያለውን የሰላም መሻሻል በመጠቀም እየተቀዛቀዘ የመጣውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል እና ሰላምን ለማምጣት የሚያግዝ እንደሆነም ነው የገለጹት።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ስፖርት በአካል የዳበረ፣በአመለካከቱ የተቃኘ እና በሥነ ምግባሩ የተመሰገነ ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ለሀገር ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ስፖርት ለሰላም ግንባታ ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባም ምክትል አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ማረልኝ ሁነኛው በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የስፖርት ዘርፉን ክፉኛ ጎድቶታል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች መቋረጣቸውን የገለፁት አቶ ማረልኝ ይህም ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዲሳልፉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች አጫጭር ውድድሮችን በማካሄድ የተቀዛቀዘውን ስፖርት እና የስፖርት ቤተሰቦችን ትስስር ለማነቃቃት እንደሚሠራም ተወካይ ኀላፊው ገልፀዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ ስፖርት ”ለሰላም እና ለልማት”በሚል መሪ መልዕክት በመከበር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከመጋቢት 23 አስከ 29/2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ኹነቶች እንደሚከበርም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!