“ቅስም ሰባሪው ዘረኝነት ባማሩ የአውሮፖ ሜዳዎች”

0
411

የዘረኝት ጥቃቶች በስፖርት ሜዳ ከመቀነስ ይልቅ መልካቸውን እየቀያየሩ በጥቁር ስፖርተኞች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀጥሏል። በተለይ እግር ኳስን የሚጫወቱ ጥቁር ተጫዋቾች በችሎታ የበላይ ከመኾን ጎን ለጎን ዘረኝነትን መጋፈጥ አሁን ግዴታቸው መስሏል፡፡ የአውሮፓ ሀገራት የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ጥቁር ተጫዋቾች ድንቅ ብቃት እና ጥበብ ቢያሳዩ የሚያጨበጭቡት ግን ለቡድናቸው እንጅ ለተጫዋቾች አይደለም። በሌላ ወገን የተሸናፊ ቡድን ደጋፊዎች በጥቁር ተጫዋቾች ጥበብ እና ክህሎት ቢደመሙ እንኳ በመንጋ ኾነው አስነዋሪ ቃላትን እና ምልክቶችን በመጠቀም ቅስም ሲሰብሩ መልከት የተለመደ መኾኑን ሪስፔክት ኦል አትሌትስ የተሰኘ ተቋም የሠራው ጥናት ያሳያል።

ተቋሙ እንደሚለው በጣልያን፣ እንግሊዝ፣ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቱጋል እና ራሽያ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች በብዛት በቆዳ ቀለማቸው እየተለዩ በግልጽ የዘረኝነት ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል። በቅርቡ በሀገረ ጣልያን የኤሲ ሚላን ቡድን ከዩዲኒዜን ጋር ሲጫወት የሚላኑ ግብ ጠባቂ ማይክ ማግናን ላይ ያደረሰውን የዘረኝነት ጥቃት ተከትሎ ጨዋታው እስከ መቋረጥ ድርሷል።

በተመሳሳይ በእንግሊዝ ሼፊልድ ዌንስዴይ ከኮቨንተሪ ሲቲ በነበራቸው ጨዋታ የኮቨንተሪው ካሴይ ፓልመር በደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት እንደደረሰበት ተናግሯል። ሪስፔክት ኦል አትሌትስ ጨምሮ እንዳተተው ስፖርታዊ ውድድር የሰላም፣ የወንድማማችነት እና የፍቅር መድረክ ነው ቢባልም አሁን ላይ ይዘቱን በመቀየር ዘረኝነት ባሰከራቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ስፖርተኞች በቆዳ ቀለማቸው እየተዘለፉ አንገታቸውን እንዲደፉ እየኾነ ነው።

በእንግሊዝ በተሠራ ሌላ ጥናት በተጫዋቾች ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት ጥቃት ከ2021/2022 ከነበረው 45 በመቶ በ2023 የውድድር ዘመን ወደ 51 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የ2022 የዓለም ዋንጫን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ በተጫዋቾች ላይ ይሰነዘሩ የነበሩ የዘረኝነት ትንኮሳዎች እና መሰል ጥቃቶች ላይ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድጋፍ ምርመራ ተደርጎ ነበር፡፡ ሃያ ሚሊዮን የሚኾኑ ‘መጋራቶች’ እና አስተያየቶች ላይ በተደረገው ምርመራ አሥራ ዘጠኝ ሺህ ገደማዎቹ ዘረኝነትን የሚያንጸባርቁ ነበሩ ተብሏል፡፡

ጥናቱ እንዳሳየው የዘረኝነት ጥቃቱ በደምሳሳው የተካሄድ ሳይኾን በተጠና እና በተቋም ደረጃ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ተጫዋቾች ሳይቀሩ የሚታዩበት ነው። ለምሳሌ፦እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2023/2024 በሩዋንዳ ሊግ በፕሮፌሽናልነት የሚጫወቱ የብሩንዲ ተጫዋቾች ግብ እንዳስቆጠሩ የብሩንዲን ሕዝብ ለአመጽ ሊያነሳሱ የሚችሉ ምልክቶችን እና ምስሎችን ለማንጸባረቅ ሞክረዋል።

የሩዋንዳ መንግሥት ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ የድርጊቱን ፈጻሚ ተጫዋቾች ከሀገሩ እስከማባረር የደረሰ ብሎም ለሌሎች የዓለም ሀገራት አርዓያ የሚኾን ርምጃ በመውሰድ ማምከኑን ልብ ይሏል ። በክልል እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ የኾኑት አቶ ብርሃኑ ሙላት ” ስፖርታዊ ዘረኝነትን ለመከላከል ከተማሪዎች እስከ የሥራ ተቋማት ሠራተኞች የሚገኘውን ሰፊ ማኅበረሰብ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ማስተማር ሁነኛ መፍትሔ ነው” ይላሉ። “ሲቀጥል ግን የድርጊቱ ፊጻሚዎች የቡድን ደጋፊዎች ከኾኑ በ እኔን ያዬህ ተቀጣ ብሂል በሕግ መጠየቅ አስፈላጊ መፍትሔ ይኾናል” ብለዋል።

አጥፊዎቹ ተጫዋቾች ከኾኑ ደግሞ አስተምሮ ከማለፍ ባለፈ ከስፖርቱ ዓለም በማባረር ሌሎችን በዚህ መንገድ ማስተማር ይገባል ይላሉ የሕግ ባለሙያው ። “ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት የሚፈጸምበትን ስታዲየምም ከጨዋታ ውጭ ከተደረገ የየከተሞቹ አሥተዳዳሪዎች የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመቆጣጠር ከፖሊስ በተጨማሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ካሜራ በመጠቀም እንዲቆጣጠሩ ይገደዳሉ ፤ ሳይንሱም የሚነግረን ይህንኑ ሐቅ ነው” ብለዋል።

እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ (ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ናቸው ) በስፖርቱ ዘርፍ የሚታዩ ትንኮሳዎች መልካቸው የተለያየ ሊኾን ይችላል። ለአብነት በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ጋር ባደረገው ጨዋታ ናይጄሪያዎቹ “ኢትዮጵያውያን ረሃብተኞች ናችሁ” በሚል አንድምታ ክብርን በሚነካ መልኩ ለኢትዮጵያውያን ተጫዎቾች እና ደጋፊዎች ዳቦ ወርውረውባቸው እንደነበርም ጠቁመዋል።

ታዲያ በዚህ መልኩ ስፖርት ለዓለም ሕዝብ ኹሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት መድረክ ነው የሚለውን መርሕ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል ባይ ናቸው። ምሁሩ አክለውም ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት እና የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሥነ-ምግባር ማፈንገጥ በየጊዜው ቢወሳም በየስታዲየሞች የሚንጸባረቀውን ዘረኝነት ግን ማስቀረት አልተቻለም ። በስፖርት ሰበብ ፖለቲካዊ መርዛቸውን የሚረጩ “የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች” በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ተግባር ሲፈጽሙ እየታዘብን ነው ብለዋል።

ስፖርት ላይ ቆመው የሌሎችን ክብር እና ነጻነት የሚጋፋ መልእክቶች እና ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች ሲተላለፉ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ግጭት የሚያጭሩ ክስተቶችን ሲያስተናግዱም የስፖርቱን የሚመሩም ይኹን መንግሥታት “የዝኾን ጆሮ ይስጠን” በማለት እያለፉት ስለኾነ ድርጊቱ በእሳት ላይ ቤንዚል እየኾነ ነው ሲሉ ኮንነውታል።

ይህ ሥርዓት አልበኝነት እና ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት እግር ኳሳዊ ፉክክሩ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ዘረኝነት በሚንጸባረቅባቸው ኹነቶች ፖለቲካዊ አንድምታው ጎልቶ እየታየ የመጣ ነው። ተጎጅዎች እና መልዕክቱ ከጥቁር ተጫዋቾች በላይ ነው፤ በእኛም ሀገር የሊግ ውድድር በይበልጥ ብሔር ተኮር የዘርኝነት ነቋራ መስተዋል ከጀመረ ውሎ አድሯልና “ሳይቃጠል በቅጠል” መባል ግድ ነው ብለዋል።

ስፖርት የዘር፣ የጎሳ እና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድበው የዓለም ቋንቋ ስለመኾኑ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አባት በሚል የሚሞካሹት ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ ሥርዓት ምክንያት ሰላም ርቆት የነበረውን የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ አንድ ያደረጉት ስፖርትን ተጠቅመው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ጠቅሰው ምሁሩ አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ ማንዴላ በዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ለሰው ልጆች ነጻነት እና መብት አስመልክተው ” ስፖርት ዓለምን ለመቀየር እና የሰው ልጆችን ኹሉ አንድ የሚያደርግ መሣሪያ ነው። የእኛ ሀገርም አሁን ከገባችበት የጸጥታ ችግር ለመውጣት ስፖርታዊ ውድድሮችን በየክሎች ማካሄድ አንዱ መፍትሔ ይኾናል።በመኾኑም ‘ስፖርትን ለሰላም’ ብለን ብንጠቀምበት አብዝተን እናተርፍበታለን ” ብለዋል።

ሜዳ ላይ የሚደርሱ የዘረኝነት ጥቃቶችን ለማስቆም ዋናው ተዋናይ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር /ፊፋ/ ነው። የአንድ ቡድን ወይም ሀገር ደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት ከሰነዘሩ ቡድናቸው በፎርፌ እንዲቀጣ ማድረግ የተሻለ ለውጥ ያመጣል የሚሉትም ፕሬዝዳንቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ናቸው።
ኢንፋንቲኖ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በሚሰነዝሩ ደጋፊዎች ላይ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የስታዲየም እግድ መጣል እና በዘረኞች ላይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ወንጀለኛነት ክስ በመመስረት መቆጣጠር አለብን” ብለዋል።

ጨክኖ አስተማሪ እርምጃ አይወስድም ተብሎ የሚተቸው ፊፋ አረአያ ኾኖ አሠራሮችን ካለበጀ እና ካልተገበረ ተወዳጁ እግር ኳስ በጥቁሮች ቂም እየተያዘበት መሄዱ አይቀርም። ከተጫዋቾች አልፎ በቤተሰቦቻቸው እና በጥቁር ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው የነውር ጥግ የሚያመጣው ጣጣም ብዙ ነው።
የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ቪኒሽየስ ጁኔር በስፔን የተለያዩ ስታዲየሞች በዘረኞች ተዘልፏል። በቅርቡ በእንባ ታጅቦ ስለዘረኝነት አስከፊነት በመናገር ነገሩ እንዳማረረው አሳይቷል።

በስፔን፣ ጣሊያን፣ቱርክ እና እንግሊዝ በመሳሰሉ ሀገራት ጥቁር ተጫዋቾች በችሎታቸው ሳይኾን በቆዳ ቀለማቸው እየተሰፈሩ መሳቂያ እና መሳለቂያ መኾናቸው የአደባባይ ሀቅ ቢኾንም የየሀገራቱ የእግር ኳሱ መሪዎችም ይሁን ክለቦች የሚወስዷቸው እርምጃዎች የለበጣ ናቸው። ይህም ዘረኞች ከስህተታቸው ከመታረም ይልቅ ቁጥራቸው እየጨመረ እንዲሄድ አድርጓል። ጥቁር ተጫዋቾችም የሚደርስባቸውን ዘለፋ መቋቋም አቅቷቸው አንገታቸውን ደፍተው ከሜዳ መውጣት እና ሲያነቡ መመልከት ለዘረኞች ዋንጫ የማንሳት ያክል ሲያስፈነጥዛቸው እየተመለከት ነው።

በሙሉጌታ ሙጨ

ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here