ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቱኒዚያው ኢስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ የእግር ኳስ ቡድን የተቋቋመው እንደ አውሮፓውያኑ በ1919 ነው። ዘንድሮ 105ኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል፡፡ አንጋፋው ቡድን በዋናነት በቀይ መደብ ላይ በቢጫ ቀለም የተለያየ ንድፍ ያረፈበት መለያ በማዘውተር ይታወቃል፡፡ ቡድኑ 60ሺህ መቀመጫ ያለው የስታድ ሃማዲ አግሬቢ ስታዲየም ባለቤትም ነው፡፡
ኢስፔራንስ ቱኒዝ በሀገረ ቱኒዝያ በድል የታጀበ ቡድን ነው፡፡ የሊግ ዋንጫን 32 ጊዜ ወስዷል፡፡ የቱኒዚያ ዋንጫን ደግሞ 15 ጊዜ አሸንፏል፡፡ ስድስት ጊዜ የቱኒዚያ ሱፐር ‘ካፕ’ን አንስቷል። ይህ ቡድን አራት የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤት ነው፡፡
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1995 ደግሞ የካፍ ሱፐር ካፕን ዋንጫ መውሰድ ችሏል፡፡ ቡድኑ የሜዲትራኒያን ዋንጫንም እንዲሁ አንስቷል፡፡ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በ51 ዓመቱ ጎልማሳ ሚጌል ካርዶሶ እየሠለጠነ ይገኛል፡፡
ኢስፔራንስ ደ ቱኒዝ 105ኛ ዓመቱን ሲያከብር ሦስት ዓላማዎችን በማንገብ ነው ያሉት የቡድኑ ዋና ጸሐፊ ፋሩክ ካትቱ የመጀመሪያውን የስፖርት ቱሪዝም በማስፋፋት የገቢ መፍጠሪያ ኢንዱስትሪ ማድረግ ነው፤ በመኾኑም በቡድኑ አካዳሚ በተለይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመረጡ ወጣቶችን አሠልጥኖ በማውጣት ተጠቃሚ ማድረግ ሲኾን ይህንንም በተግባር ማሳካቱ እየተነገረ ነው፡፡
ሁለተኛው የሀገሪቱን ገጽታ በዓለም ሕዝብ ዘንድ መገንባት ሲኾን ላለፉት 105 ዓመታትም እንደተገበረው ተጠቁሟል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሀገሪቱን ከሁሉም ሀገራት ጋር ስፖርቱን አስታክካ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርን መፍጠር እንደኾነ አፍሪካን ፉትቦል እና ስፖርቲቭ ዴ ቱኒዝ በድረ ገጻቸው ዘግበዋል፡፡
ስለኾነም የኢስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ የእግር ኳስ ቡድን ከማንኛውም ሀገር ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ የሀገሪቱን ገጽታ በመሸጥ ተጠቃሚ በማድረግ የተሳካለት ቡድን መኾኑን በ105ኛ ዓመቱ በዓል አከባበር ወቅት ተነግሯል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!