“እግር ኳስ ውጤታማ ስትኾኑ ያስከብራችኋል” ቺያማካ ናዶዚ

0
277

ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ አፍሪካን በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሚወክሉት አራት ሀገራት አንዱ የናይጄሪያ የሴቶች ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ በቅጽል ስሙ ጭልፊት በመባል ይጠራል፡፡ የዚህ ቡድን የብረት ዘቧ ደግሞ ቺያማካ ናዶዚ ናት፡፡ ተጫዋቿ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ታሕሳሥ 08/2000 “ሚበል” በተባለች ከተማ ተወለደች፡፡ የአንድ ሜትር ከ80 ሴንቲ ሜትር ለግላጋዋ ቺያማካ ወንድሞቿ ጋር እግር ኳስ በመጫወት ነው ያደገችው፡፡

“ከታላላቅ ወንድሞቼ ጋር ስጫዎት በእድሜ ታናሽ ነበርሁ” ምትለው ቺያማካ ናዶዚ ሜዳ ላይ ጉዳት እንዳይደርስባት በግብ ክልል ውስጥ ትጫወት ነበር፡፡ “አንድ ቀን ከወንዶቹ ጋር ስጫዎት የእኛ ቡድን 13 ግብ ተቆጠረብን፡፡ በወቅቱ ግብ ጠባቂያችን በጣም ደክሞት ነበር። እሱን ለመርዳትም ግብ ጠባቂ ኾንሁ” ብላለች፡፡

በዚህ መልኩ የጀመረችውን ግብ ጠባቂነት እያደር እየወደደችው ሄደች፡፡ በቤቷ እራሷን ግብ ጠባቂ በማድረግ ኳስ እያነጠረች እና ከግድግዳ ጋር እያጋጨች ትይዝ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት በወንዶቹ ቡድን ሳይቀር በረኛ እየኾነች በመጫዎት ችሎታዋን አዳበረች፡፡
ቀስ በቀስም በኢሞ ቀበሌ የታዳጊ ሴቶች ቡድን ግብ ጠባቂ ኾና ተመረጠች፤ ድንቅ ብቃቷንም አስመሰከረች፡፡

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2016 በናይጀሪያ ሴቶች ፕሪሜየር ሊግ የሚሳተፈውን ሪቨርስ አንግልስ ቡድን በመቀላቀል ተጫወተች፡፡ ከ2020 ጀምሮም የፈረንሳዩን ፓሪስ ኤፍ ሲ ቡድን አስፈርሟት እየተጫዎተች ትገኛለች፡፡ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መኾኗም እየተነገረ ነው፡፡

የናይጄሪያ የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ጭልፊት) ቋሚ ግብ ጠባቂ የኾነቸው ቺያማካ ናዶዚ “አባቴ እግር ኳስ እንድጫወት አይፈልግም ነበር፡፡ ስለኾነም ወደ ሜዳ እንዳልሄድ በማስጠንቀቅ ይከለክለኛል፤ በሌላ በኩል እናቴ የአባቴን ሃሳብ በመቃወም ከጎኔ ቆማለች” ስትል ተናግራለች።
“እግር ኳስ ልጫዎት ስሄድ አባቴን ለጉዞ እንደላከችኝ በመዋሸት እንድጫዎት ታደርገኛለች፡፡ እናም ለስኬቴ መሰረት እናቴ በመኾኗ አመሰግናታለሁ” ብላለች፡፡

“ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ ሽልማቴን ሲያይ ደስተኛ ኾኗል፡፡ እናንተም በመንገዳችሁ ላይ እንቅፋት ቢኖርም ጠንክራችሁ መሥራታችሁን ቀጥሉበት። ውጤት እና ገንዘብ ሲመጣ ትከበራላችሁ” በማለት ልጃገረዶችን አነቃቅታለች፡፡ በአባቷ ሐሳብ ሳይኾን በራሷ መንገድ በመሄዷም በ23 ዓመቷ ሞሮኳዊቷን ኳሷ ኻዲጃ ኤል-ርሚቺ እና ደቡብ አፍሪካዊቷን አንዲሌ ኦላሚኒ በማሸነፍ የ2023 የካፍ የሴቶች ምርጥ ግብ ጠባቂ በመኾን ተሸለመች።

ሽልማቷን እንደተቀበለችም የናይጄሪያ የእግር ኳስ ኀላፊዎች ለሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ድጋፍ እና ክብካቤ ባያደርጉልን ኑሮ “እኔ የናይጄሪያ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ድምር ውጤት አልኾንም ነበር” በማለት አመስግናለች፡፡ “አፍሪካውያን ልጃገረዶች እግር ኳስ ለመጫወት ሕልም ካላችሁ እመኑኝ ጠንክራችሁ ከሠራችሁ ሕልማችሁ እውን ይኾናል፤ እኔን እዩኝማ! እኔ በሐብትም በዝናም ከፍ ብያለሁና” በማለት መክራለች፡፡ “እግር ኳስ ውጤታማ ስትኾኑ ያስከብራችኋል” ስትልም ተናግራለች ቺያማካ ናዶዚ። በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ በሴቶች እግር ኳስ አፍሪካን የሚወክሉ ሀገራት ናቸው፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here