ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡ ቀን 9 ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከ ሀምበርቾ ይጫወታሉ፡፡ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከወላይታ ድቻ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
ሀምበርቾን የሚገጥሙት ወልቂጤዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባሕር ዳር ከተማ ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደዋል፡፡ይሁንና በአምስተኛው ሳምንት ሻሸመኔ ከተማን አሸንፈው ነጥባቸውን አምስት አድርሰዋል፡፡ ይህም የወልቂጤ ከተማ ትልቁ ክፍተት የነበረው የማጥቃት ክፍሉ ከጨዋታ – ጨዋታ ወደ ግብ ማስቆጠር መመለሱን አመላክቷል።
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ማስመዝገብ የቻለው ሀምበሪቾ ደግሞ ከተከታታይ ሽንፈት ለማገገም ይጫወታል። በጨዋታውም በአመዛኙ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ይተገብራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እና መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ያለ ድል ለሀምበሪቾ አይበጀውም፤ ነጥብ ያስፈልገዋልና፡፡ የሀምበሪቾ የቀኝ እና የግራ መስመር አጥቂዎች ጠንካሮች ናቸው፡፡ በዚህ መስመር የሚያሻግሩት ኳስ የፊት አጥቂዎች ግብ እንዲያስቆጥሩ ያግዛቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ይህን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፡፡ አብዱ አሊ እና ደረጄ አመራ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል፡፡ ሙሉቀን ያረጋል ደግሞ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ናቸው።ምሽት 12 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ሀምበሪቾን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ዐፄዎቹ በአስራ ሁለት ነጥብ በ4ኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ ለመጠጋትም የጦና ንቦችን ዛሬ ይገጥማሉ። ዐፄዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻል እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ ከውጤት ባሻገር አጨዋወቱ ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል።
በተለይም ደግሞ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው ጠንካራው የተከላካይ መስመር የቡድኑ ዋነኛው የብረት ዘብ ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ከፈጣኖቹ የወላይታ ድቻ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ዐፄዎቹ ምንም እንኳ እንደሚፈጥሯቸው በርካታ ዕድሎች በዛ ያሉ ግቦች ባያስቆጥሩም የቡድኑ የአማካይ ክፍል ጨዋታ ከመቆጣጠር አልፎ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።
ዐፄዎቹ በዛሬው ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ የሚሰጥ የአማካይ ጥምረት ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ጥሩ የመሀል ሜዳ ፉክክር ያለበት ጨዋታ ይኾናል ተብሎ ይገመታል። ኢትዮጵያ መድንን አንድ ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ከድል የራቁት ወላይታ ድቻዎች በስምንት ነጥብ በ8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
የጦና ንቦቹ ምንም እንኳ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ቢገኙም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ምንም ድል አላስመዘገቡም። ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ማሳካት የቻለው ሁለቱን ብቻ ነው። እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ በዛሬው ጨዋታ ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች ለመላቀቅ ምንም ሽንፈት ካላስተናገደው ፋሲል ከነማ ጋር ይጫወታል።
የጦና ንቦቹ በፊት መስመር ላይ ያላቸው የአፈፃፀም ችግር ዋነኛው የቡድኑ ድክመት ተደርጎ ይወሰዳል። የአማካይ ክፍሉ ምንም እንኳ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖው በመጠኑ ቢቀንስም የግብ ዕድሎች በመፍጠር በኩል ግን አልቦዘነም፡፡
በውድድር ዓመቱ ከአንድ ጨዋታ ውጭ በተቀሩት ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር አለመቻላቸው የቡድኑ የአፈፃፀም ችግር ማሳያዎች ናቸው። በዛሬው ጨዋታም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ የተከላካይ ክፍል ያለውን ቡድን ስለሚገጥሙ ፈተናው ቀላል አይኾንላቸውም።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 12 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ፋሲል ከነማ ሰባት ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አራት ጊዜ አሸንፈዋል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ፋሲካ የኋላሸት እና ኤፍሬም ኅይለማርያም ይህን ጨዋታ ይመራሉ፡፡ ባሕሩ ተካ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመኾን ለጨዋታው ተመድበዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!