በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ ውድድር መሳተፏን ያረጋገጠችው ጆርጅያ

0
367

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጆርጅያ ከሶቭየት ኅብረት ተገንጥለው ራሳቸውን ከቻሉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በአውሮፓ እና እስያ ጫፍ ላይ የምትገኘው ጆርጅያ አሁን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት የብሪታኒካ መረጃ ያስረዳል። በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ለመሳተፍ ብዙ ጥረት ያደረገችው ትንሿ ሀገር በመጨረሻ ግሪክን በመለያ ምት በማሸነፍ ህልሟን እውን አድርጋለች።

እግር ኳስ የሚወደድባት ሀገሪቱ በትልቅ ውድድር ለመሳተፍ የዓመታት ሙከራዎችን አድርጋለች። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1990 የመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዋን ያደረገችው ጆርጅያ በትልቅ መድረክ ለመሳተፍ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፋለች። በአውሮፓ እና በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለማድረግ ጆርጅያ 15 ሙከራዎችን አድርጋለች። በእነዚህ ሙከራዎች ጆርጅያውያን ከውድቀታቸው እየተማሩ በመጨረሻ አንገታቸውን ቀና አድርገው አዲስ የእግር ኳስ ታሪካቸውን መጻፍ ጀምረዋል።

ለ1996ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ለማለፍ በ1994 ለመጀመሪያ ጊዜ የነጥብ ጨዋታዋን ያደረገችው ጆርጅያ ከ30 ዓመታት በኋላ ራሷን የውድድሩ ተሳታፊ አድርጋለች። ያኔ በሞልዶቫ 1 ለ 0 ተሸንፋ የነበረ ሲኾን ትናንት ከግሪክ ጋር የነበረባትን ጨዋታ በመለያ ምት አሸናፊ በመኾን ለጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ትኬት ቆርጣለች።

ውጤቱን ተከትሎ በሀገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ የደስታ ጊዜ ኾኗል። ጨዋታው መጠናቀቁን ተከትሎ ስታድየም ውስጥ የተጀመረው ፌሽታ በሀገሪቱ ዋና ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች ደምቆ አምሽቷል። የፊታችን ሰኔ በሚጀምረው የአውሮፖ ዋንጫ ጆርጅያ ፖርቱጋል፣ ቱርክ እና ቼክ በሚገኙበት ምድብም ተደልድላለች።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here