ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አፍሪካውያን በኹሉም ዘርፍ እንደሚችሉ ለዓለም ሕዝብ ትምህርት የሰጡበት ዝግጅት ነው። የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በአፍሪካ ኅብረት የስፖርት ምክር ቤት አሥተባባሪነት በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ውድድር ነው።
ውድድሩ ለአህጉሩ የአትሌቲክስ ልኅቀት፣ የባሕል ውርርስ፣ ቅርስ ትውውቅ እና አንድነት መማማሪያ መድረክ በመኾን ትልቅ ሚና ይወጣል። የአህጉሩ ወጣቶች በትምህርት፣ በፆታ እኩልነት እና በማኅበራዊ መስተጋብር ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ፤ አፍሪካዉያን ወንድማማችነት ከፍ የማድረግ ሚናውም ከፍ ያለ ነው።
13ኛውን የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሰሞኑን በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና አዘጋጅነት ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል። በድግሱ ከ53 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 5ሺህ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈዋል። የተለያዬ የሙያ ዘርፍ ያላቸው ታዳሚያን፣ ከተለያዩ አህጉራት የመጡ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ባለሙያዎች እና የስፖርት ቤተሰቦች ጋናን አድምቀውት ሰንብተዋል።
ሀገሪቱ ለዝግጅቱ 195 ሚሊዮን ዶላር ለመሰረተ ልማት ግንባታ ወጭ ማድረጓን የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል። ነገር ግን ጋናዉያን ከውድድሩ ብዙ ማትረፋቸው እየተነገረ ነው። የመጀመሪያው ጥቅምም ጋና ለዝግጅቱ በማለት የገነባቻቸው ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሀገሪቱ ቀሪ ሀብቶቿ መኾናቸው ነው። በቦርቴማን ከተማ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከል እንዲገነባ ሰበብ ኾኗል። የአክራ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም 50ሺህ መቀመጫ እንዲኖረው ኾኖም ታድሷል። ለስፖርተኞች ማረፊያ የሚኾኑ አዳዲስ መንደሮች ተገንብተዋል፤ ነባሮቹም በዘመናዊ መልኩ ታድሰዋል ብለዋል የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ሙስጠፋ ዑሲፉ። “እያደርን ደግሞ የቦርቲማን የስፖርት ኮምፕሌክስን ወደ አፍሪካ ስፖርት ዩኒቨርሲቲነት ለመለወጥ እንድናቅድ አነሳስቶናል” ነው ያሉት።
“ጋና የመላው አፍሪካ ጨዋታዎችን በማዘጋጀቷ በሰፊው ተጠቃሚ ኾናለች” ያሉት ሚኒስትሩ በጨዋታዎች ሰሞን የዋትስ አፕ፣ የፌስቡክ፣ የኤክስ፣ የኢንስታግራም፣ የቲክ ቶክ እና የኢሜል ተጠቃሚዎች ሁለመናቸውን ሀገሪቱ ላይ አድርገው ቆይተዋል ብለዋል።
በሁለት ሳምንት ጊዜያት ውስጥም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚገመት የዓለም ሕዝብ በቴሌቭዥን እና በኦንላይን ጨዋታዎችን ተከታትሏል፤ ስለጋና ብሎም አፍሪካ ዘርፈ ብዙ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል፤ በዚህም ጋናን በስፋት በማስተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ ጨዋታው የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
ውድድሩ ለሀገሪቱ ይዞላት ከመጣው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ ምጣኔ ሀብታዊ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከመቼውም በላይ የፍራፍሬ ምርት ማለትም ኮኮናት፣ አናናስ፣ ሲትረስ፣ ሙዝ እና ፓፓያ ወደ አውሮፓ ሀገራት በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ እንዳገኘች ተናግረዋል።
ጋና በቱሪዝም ዘርፍ ባሕሏን በተለይም ውዝዋዜዋን፣ ሙዚቃዋን፣ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጧን ለውጭው ዓለም ማስተዋወቅም ችላለች ብለዋል ሚኒስትሩ ።
በጋና አክራ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ኣናን ማቷን (ዶ.ር) እንዳሉት በጨዋታው ሳምንታት ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዶላር ወደ ጋና ባንኮች ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ገቢ ኾኗል ብለዋል። በርካታ የአውሮፕላን ምልልሶች ተካሂደዋል። የቀጥታ የስልክ ልውውጦች እንዲሁም የጽሑፍ መልዕክቶች ነበሩ። የታሸጉ ምግቦች እና መድኃኒቶች እንዲሁም ከሀገር ምርት ባለፈ ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ባለ አንድ ሊትር ጥራቱን የጠበቀ የመጠጥ ውኃ ወደ ሀገሪቱ ገብቶ ገበያ ላይ ውሏል።
የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም እንደ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የትራንስፖርት አውታሮች ገበያቸው ጥሩ ኾኖ መሰንበቱን ምሁሩ አብራርተዋል። ይህ ሁሉ ተደማምሮም ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ አግኝታበታለች፤ ራሷንም አስተዋውቃበታለች ብለዋል።
ምሁሩ አያይዘውም ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም በመጠናቀቁ የውጭ አልሚ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በተለያዩ አውታሮች ላይ ቀጥታ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አደፋፍሯቸዋል።
በጠቅላላው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አፍሪካውያን በኹሉም ዘርፍ እንደሚችሉ ለዓለም ሕዝብ ትምህርት የሰጡበት እንደነበር ምሁሩ መናገራቸውን የጋና የዜና ምንጭ ጂ.ኤን.ኤ ዘግቧል።
በፓንች ስፖርትስ ኤክስትራ ዘገባ መሠረት በ13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ 101 ወርቅ፣ 46 ብር እና 42 ነሐስ በድምሩ 189 ሜዳሊያዎችን በመስብሰብ አሸናፊ ኾናለች። ናይጄሪያ በ47 ወርቅ፣ 33 ብር እና 40 ነሐስ በድምሩ በ120 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
ደቡብ አፍሪካ በ32 ወርቅ፣ በ32 ብር እና በ42 ነሐስ በድምሩ በ106 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በ13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ብቻ 47 ወንድ እና 40 ሴት በድምሩ 87 አትሌቶችን አሳትፋለች። በአትሌቲክስ ብቻ 7 ወርቅ፣ 7 ብር እና 4 ነሐስ በድምሩ 18 ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ በዘርፉ ከናይጀሪያ ቀጥላ 2ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። አጠቃላይ ውድድሩን ደግሞ ስምንተኛ ኾና አጠናቃለች።
በተለይ በአትሌቲክስ የተመዘገበው ውጤት የሚያኮራ ነው። ከውጤቱ በተጨማሪም 15ኛውን የአፍሪካ ጨዋታ አዲስ አበባ ለማዘጋጀት ፍላጎት አሳይታለች ተብሎ ከጋና የተሰማው ወሬ ለሀገሪቱ የስፖርት እድገት እና ቱሪዝም መነቃቃት መልካም የሚባል ነው። የሚሳካ ከኾነም ከጋና ተምረን “የምናተርፈው ብዙ ሊኾን ይችላል”።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!