በሻምፒዮንስ ሊጉ ቀሪ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ቦታዎችን ለማግኘት የሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።

0
319

ባሕርዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ስምንቱን የሚቀላቀሉ ቀሪ ሁለት ቡድኖችን የሚለዩ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። የጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከሆላንዱ ፒስቪ አይንዶቨን፣ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የመልስ ጠዋታቸውን የሚያከናውኑ ይኾናል።

አትሌትኮ ማድሪድ እና ኢንተር ሚላን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በኢንተር 1 ለ 0 አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው። የዛሬው የመልስ ጨዋታ በአትሌቲኮ ሜዳ ይከናወናል። የዲያጎ ሴሞኒው ቡድን ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንዲኹም ኢንተር ሚላን የያዘውን የተሻለ እድል አስጠብቆ ሩብ ፍጻሜው ላይ ለመገኘት ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ዶርትሙንድ ከፒስቪ ያደረገውን የመጀመሪያውን ጨዋታ አንድ እኩል አጠናቋል። የዛሬውን ጨዋታ በሜዳው የሚያከነውን በመኾኑ የተሻለ እድል አለው።

ትናንት ምሽት በተካሄዱ ጨዋታዎች አርሰናል እና ባርሴሎና ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል። አርሰናል በመጀመሪያው ጨዋታ በፖርቶ 1 ለ 0 ተሸንፎ ነበር። በመልሱ ጨዋታ በተመሳሳይ ውጤት አርሰናል ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች ብርቱ ፍክክር ባደረጉበት ጨዋታ በመጨረሻ አርሰናል በመለያ ምት በማሸነፍ ከ 14 ዓመታት በኋላ ሩብ ፍጻሜ ለመድረስ በቅቷል።

ባርሴሎናን ከናፖሊ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ በባርሴሎና 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ግጥሚያቸው አንድ እኩል ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ባርሴሎና በደርሶ መልስ 4 ለ 2 ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ባየር ሙኒክ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሪያል መድሪድ፣ ፒስጅ፣ አርሰናል እና ባርሴሎና እስካኹን የሩብ ፍጻሜ ቦታቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች ናቸው። ቀሪ ሁለት ቡድኖች ደግሞ ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይለያሉ።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here