“በአፍሪካ ደረጃ የቡድን መስፈርትን አሟልተው ከተመዘገቡ ሁለት የሀገራችን ክለቦች አንዱ ባሕር ዳር ከተማ”

0
441

ባሕርዳር: መጋቢት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በ1973 ዓ.ም እንደተቋቋመ ከይፋዊ የማኅበረሰብ ትስስር ገጹ ላይ መረዳት ይቻላል። ቡድን ሲቋቋም ይዞት የተነሳው ዓላማ በወጣቶች ስብስብ የስፖርት ቤተሰቡን አያዝናና የከተማዋን ገጽታ መገንባት ነው። በተጨማሪም ለበርካታ ግለሰቦች እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የገቢ ምንጭም ፈጥሯል።

የእግር ኳስ ቡድኑ በከተማ ደረጃ በአንደኛ ዲቪዚዮን፣ በሀገር አቀፍ ውድድር ደግሞ በብሔራዊ ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ ተጫውቷል፤ አኹን በፕሪሜየር ሊጉ እየተሳተፈ ይገኛል።
ቡድኑ እያደር በሳየው ዕድገት ከተማዋ እና ከክልሉ ባለፈም የኢትዮጵያን ገጽታም በበጎ ማስጠራት ችሏል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ2015 የውድድር ዘመን እስከ መጨረሻው መርሐ ግብር የዋንጫ ተፎካካሪ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኾኖ በመዝለቅ አይረሴ የውድድር ዓመት አሳልፏል። በአፍሪካ የክለቦች የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ኾኖ በመቅረብ ሀገርን፣ ክልልን እና ባሕር ዳር ከተማን ማስተዋወቅ የቻለ ቡድንም ኾኗል።

የጣናው ሞገድ በ2016 የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ዘመን አጀማመሩ ጥሩ ነበር። ነገር ግን እያደር በተለይ በመጀመሪያው ዙር መርሐ ግብር ውጤት ርቆት ተመልክተናል። በተለይ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፈበት አጋጣሚ በብዙዎች ዘንድ “ለምን?” የሚል ጥያቄ አስቶ ነበር።

አቶ ዘላለም ጌጤነህ የስፖርት ሳይንስ መምህር ናቸው። በተለያዩ ቡድኖች ከብሔራዊ ሊግ እስከ ፕሪሜየር ሊግ ደረጃ የተጫወቱ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የታዳጊ እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት የባሕር ዳር ከነማ ቡድን በ2016 የውድድር ዘመን የአጥቂው ክፍል በመሳሳቱ እና ከሜዳ ባሻገር የተጫዋቾች ቁርጠኛ አለመኾን ውጤት እንዲያጣ አድርጎታል ባይ ናቸው። ባለሙያው የቡድኑ መሪዎች የተዳከመውን ክፍል ቶሎ ለይተው ማጠናከር ሲገባቸው ብዙ ‘አስታመውታል’ነው ያሉት።

አቶ ዘላለም አክለውም ከስፖርታዊ ሥነ ምግባር ውጪ የሚኾኑ ተጫዋቾችን በወቅቱ በመምከር፣ በመገሰጽ፣ በማስጠንቀቅ አልኾን ሲልም የሚያስተምር እርምጃ በመውሰድ የቡድኑን ጥንካሬ መመለስ እንደሚቻል አንስተዋል።

መሰል ነገር ሲከሰት የአንድ ተጫዋች ብቻ እንዳልኾነ ጠርጥሮ ተጫዋቾችን ፈጥኖ በማወያዬት እልባት መስጠት የቡድን መሪዎች ብልጠት ነው። የጣና ሞገዶቹ እንደዚያ ባለመድረጋቸው ለተከታታይ ሽንፈት ተዳርገዋል ሲሉ የግል ምልከታቸውን አንስተዋል።

በሱፐር ስፖርት የእግር ኳስ ተንታኝ የኾነው ዮናስ አዘዘ ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ ለትልቅ ደረጃ ሲጠበቅ በ2016 የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ተዳክሞ አይተነዋል። ምክንያቱ ደግሞ የተጫዋቾች የግል ብቃት ሲወርድ እግር በግር ተከታትሎ ማስተካከል ባለመቻሉ ነው።

ተጫዋቾች በመልበሻ ቤት ያላቸው ሥነ ምግባርም ጥሩ አለመኾን ቡድኑ እንዲዳከም አድርጎታል።ስለዚህ ቡድኑ ያለበትን ውስን ችግር በማረም ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፤ እርሾ ስላለው ብሏል።

የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድን ሰብሰቢ አብርሃም አሰፋ ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ ለቡድኑ ውጤት ማጣት አንዱ ምክንያት በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ወደ ጨዋታ መግባቱ ነው።
በውድድር ዘመኑ መባቻ ላይ የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች በሚፈልጉት ልክ ማግኘት አለመቻላቸው ቡድኑ በኹሉም ቦታ ጠንካራ እንዳይኾን አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።
“በጠቅላላው የውድድር ዓመቱ ሲጀመር ቡድኑ የተሟላ አልነበረም፣ ለዚህም ነው አሸናፊ ያልኾነው “ብለዋል አቶ አብርሃም።

የቡድኑ ቦርድ በ2011ዓ.ም ሲቋቋም በአምስት ዓመታት ውስጥ በሀገር ውስጥ ውድድር ተፎካካሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ መኾን እንዲኹም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መወዳደር የሚሉ ግቦችን አሰቀምጠን አሳክተናል ብለዋል የቦርድ ሰብሳቢው። “ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካ ደረጃ የቡድን መስፈርትን አሟልተው ከተመዘገቡ ሁለት ቡድኖች አንዱ ባሕር ዳር ከነማ ነው። ይህም ቡድኑ የደረሰበትን ስኬት ያሳያል”ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ቡድንን ወደ ቀደመ ጥንካሬው ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን የክለቡ ሥራ አሥኪያጅ ለዑል ፈቃደ ለአሚኮ ስፖርት ከዚህ በፊት ሀሳብ መስጠታቸው ይታወሳል። ቡዱኑ ውስጥ ያለውን የአጥቂ ተጫዋቾችን እጥረት በዝውውር መሙላት ትኩረት እንደሚሰጠውም አስምረውበት ነበር።

አኹን ሦስት የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለዋል። ሥራ አስኪያጁ ጠንካራው ባሕር ዳር ከተማ በቅርቡ ይመለሳል ብለው ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ቡድኑ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here