ባሕርዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር የ2016 ዓ.ም የካራቴ ሻምፒዮና መካሄድ ጀምሯል። 10 የስፖርት ቤቶች በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ሲኾን በተላያዩ ዘርፎች የሚገኙ ታዳጊዎች ውድድራቸውን በካራቴ፣ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፣ በውሹ እና በወርልድ ቴኳንዶ ያከናውናሉ።
መሰል ውድድሮች መከናወናቸው የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው የገለጹት አሠልጣኞች ከተማ አሥተዳደሩ በቀጣይ በስፋት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው በከተማዋ 27 የቤት ውስጥ ስፖርት ቤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ኀላፊው ስፖርተኞቹ ከከተማዋ ባለፈ ሀገራቸውን በመወክል የተለያዩ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
አምራቹ ወጣት ወደ ስፖርት እንዲመጣ ለማድረግ መምሪያው በትኩረት እንደሚሠራም አቶ ሰይድ ተናግረዋል።የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድም ኾነ ሌሎች ተግባራቶችን ለማከናወን ሰላም አስፈላጊ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የደሴ ከተማ ወጣት ሰላም ወዳድ መኾኑን እያሳየ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
በከተማዋ የቤት ውስጥ ስፖርትን ለማስፋፋት ከተማ አሥተዳደሩ ለአሠልጣኞች የብቃት ማሻሻያ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎችም አስፈላጊ እገዛዎችን እንደሚያደርግ አቶ ሽመልስ ጠቁመዋል።በውድድሩ ላይ በከተማዋ የሚገኙ የካራቴ ሠልጣኞች፣ የስፖርቱ ደጋፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!