ባሕርዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትልቁ የአውሮፓ ክለቦች የውድድር መድረክ ሻምፒዮንስ ሊግ አኹን ለግማሽ ፍጻሜ የሚደርሱ ቡድኖችን የሚለዩ ግጥሚያዎችን አያከናወነ ነው።
ዛሬ ምሽት ሁለት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። የአምናው የውድድሩ የዋንጫ ባለቤት ማንቸስተር ሲቲ ከዴንማርኩ ኮፐን ሀገን እንዲኹም ረያል ማድሪድ ከአርቢ ሊፕዚንግ ይጫወታሉ።
በመጀመሪያ ዙር ሲቲ ተጋጣሚውን 3 ለ 1 በመርታት የማለፍ እድሉን በእጁ አስገብቷል።
የጋርዲዮላው ቡድን በአንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም ይኹን በሻምፒዮንስ ሊጉ በመልካም ግስጋሴ ላይ ይገኛል። ከሜዳው ውጭ ያሸነፈው ኮፐን ሀገንም ቢኾን ሲቲን የሚገዳደር ቡድን አይደለም። አንደ ቢቢሲ ዘገባ ማንቸስተር ሲቲ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሉ ያለቀ ነገር ነው ፤ በእርግጥ በእግር ኳስ አለቀ የሚባል ግጥሚያ የለም የሚለው እንዳለ ኾኖ።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ውጤታማው ክለብ ሪያል ማድሪድ አርቢ ሊፕዚንግን ይጋብዛል። ነጮቹ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ 1 ለ 0 በመርታታቸው የተሻለ ግማሽ ፍጻሜውን የመቀላቀል እድል አላቸው።
ትናንት ምሽት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ባየርሙኒክ እና ፒስጅ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል። ሙኒክ ላዚዮን 3 ለ 0 ሲረት ሀሪኬን ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ቶማስ ሙለር ቀሪዋን ግብ ለክለቡ አስገኝቷል። በመጀመሪያው ጨዋታ ጣሊያን ላይ ላዚዮ ሙኒክን 1 ለ 0 ረቶ የነበረ ቢኾንም የጀርመኑ ክለብ በድምሩ 3 ለ 1 አሸንፎ ስምንቱ ውስጥ ተገኝቷል።
በሌላ የትናንት ምሽት ጨዋታ ፒስጅ ሪያል ሶሴዳድን አሸንፏል። ኪያሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን ባስቆጠረበት በዚህ ጨዋታ ፒስጅ 2 ለ 1 ነው ያሸነፈው። የመጀመሪያውን ጨዋታ 2 ለ 0 የረታ ሲኾን በድምሩ የ4 ለ 1 ድል ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!