ባሕርዳር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አትሌት አበበች አፈወርቅ ከደብረብርሀን ተነስታ አኹን በትልልቅ ውድድሮች እየተሳተፈች ነው።
“ማን ይናገር የነበረ ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና ከሰሜን ሸዋ መርሐቤቴ ከተማ የተገኘችው ይህችው አትሌት የትምህርት ቤት እና የአካባቢ ጓደኞቿ “ምን መኾን ትፈልጋላችሁ?” ሲባሉ ‘ዶክተር ፣ፓይለት…”ይሉ እንደነበር ታስታውሳለች።
እሷ ግን በድፍረት አትሌት መኾን እንደምትፈልግ ከመናገሯ ባለፈ ጠንክራ በመሥራት ሕልሟን እውን ማድረግ እንደምትችል እራሷን ማሳመኗንም ታስታውሳለች። ስለኾነም የነገን ብሩሕ ቀን አስባ በምቾት አልባ ሥፍራዎች ኹሉ ሮጣ አኹን ህልሟን እየኖረች ነው።
ከመደበኛ ትምህርቷ ጎን ለጎን ጠዋት፣ ቀን እና ምሽት ላይ ልምምዷን በግል በመቀጠሏ በቅን ሰዎች ድጋፍ በፕሮጀክት ታቅፋ እንድትሠለጥን ዕድሉን ማግኘቷን ለዚህ እንዳበቃት ተናግራለች።
በትጋቷም በብሔራዊ ቡድን ተመርጣ የሀገሯን መለያ ለብሳ በዓለም አደባባይ በ10ሺህ እና በግማሽ ማራቶን በኔዘርላንድስ መወዳደር ችላለች።
በጣልያን፣ በኮሎምቢያ እና በስፔን ሀገራት በመወዳደር በርካታ አመርቂ ውጤቶችንም አስመዝግባለች። አትሌቷ ስለውጤቷ ስትጠየቅ በፕሮጀክት እና በክለብ ታቅፋ መሥራቷ ለውጤት እንዳበቃትም ነግራናለች።
“ሰሜን ሸዋ ለአትሌቲክስ የተመቼ አካባቢ ነው ” የምትለው አበበች እንደ እሷ ኹሉ ሌሎች ታዳጊዎችም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እና ለስኬት በቅተው የሀገርና የወገን መኩሪያ ይኾኑ ዘንድ ክለቦች ሊበዙ ይገባል ብላለች።
የአትሌቲክስ ማዕከላቱ በአግባቡ ከተሠራባቸው ፋይዳቸው ከፍተኛ መኾኑን በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል አሠልጣኝ የኾነው አማረ ሙጨ ይናገራል። በአኹኑ ጊዜ በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል 40 ሴት እና 40 ወንድ በድምሩ 80 አትሌቶችን እያሠለጠነ እንደሚገኝም ጠቁሟል።
” የአማራ ክልል መልከዓምድር እና የአየር ፀባይ ዓይነቱ ይለያያል እንጅ ለኹሉም የስፖርት ዓይነት ጥሩ የኾነ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ነው የሚለው አማረ “ለምሳሌ፦ ደብረ ብርሃን እና አካባቢው ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ ስለኾነ በርካታ አትሌቶች ወጥተውበታል ባይ ነው።
አትሌት ብርሃን፣ ከልክሌ፣ ስንታየሁ ፣ እታገኝ ፣ አበበች እና ሌሎችም በማዕከሉ ሠልጥነው የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸውን የጠቀሙ ናቸው ብሏል። አትሌቶቹ በሚያገኙት ገንዘብም በልማት እየተሠማሩ እና የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ስለመኾናቸው ተናግሯል።
እንዲህ የተነቃቃው እና ሀገርን የወከሉ ወጣቶችን ያፈራው የአማራ ክልል የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ አኹን መቀዛቀዝ እየታየበት ነው። አሠልጣኝ የኾነው አማረ ሙጨ “አኹን ነባር የአትሌቲክስ ክለቦች እየፈረሱ ናቸው፤ ክለብ ባለመኖሩ ደግሞ ወቅቱን የጠበቀ ውድድር ስለማይደረግ ባለሙያዎችም ገሸሽ እንዲሉ አድርጓቸዋል። የክልሉ የአትሌቲክስ ውጤት ከዓመት ዓመት የመዳከም ምክንያቱ የክለቦች ቁጥር እየቀነሰ አኹን ላይ “የለም” ከሚባልበት ደረጃ መድረሱ ነው” ብሏል አሠልጣኙ።
አሠልጣኙ ጨምሮ እንደገለጸው በክልሉ የአትሌቲክስ ክለብ በብዛት ባለመኖሩ ከማሠልጠኛ ማዕከላት የሚያሰለጥኑ ልጆችን ወስደው የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ክልሎች ናቸው ። ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ ሌሎች ታዳጊዎች በብዛት ‘እንዳይፈሩ’ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል እንዳልኾነ አማረ በቁጭት ተናግሯል።
አሠልጣኝ አማረ አክሎም ቀደም ባሉት ጊዜያት ክልሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመደገፉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ይላል። ለምሳሌ፦ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ መንግሥት፣የልማት ድርጅቶች፣ ባለሐብቶች እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በክልሉ አሥተባባሪነት አትሌቲክሱን ይደግፉ ስለነበር ጥሩ ውጤት ይመዘገብ ነበር።
“ከ2015 ጀምሮ ግን በጸጥታ ችግር ውድድር ማዘጋጀት ባይችሉ እንኳ በሌሎች ክልሎች በሚዘጋጁ ውድድሮች በተጋባዥ ተወዳዳሪነት የምንሳተፍበትን ዕድል ማመቻቸት ባለመቻሉ አትሌቶች እንዲዘናጉ እና የዕለት ተዕለት ተስፋቸው እንዲቀንስ አድርጓቸዋል ነው ያለው።
ሌላው ደግሞ እንደ ፈረስ ቤት፣ ቲሊሊ፣ ሰከላ፣ ደባርቅ ያሉ ማዕከላት ግንባታቸው ቢጠናቀቅም ሥልጠና እየሰጡ አይደሉም። ይህ ለዘርፉ የተሰጠውን የትኩረት ማነስ ያመላክታል፤ ለተንታ፣ ጉና፣ ደብረ ብርሃን እየተደረገ ያለው ድጋፍ እና እገዛም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው። ስለኾነም በቅርቡ ክልሉ በጃንሜዳ ዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ውድድር ቢካፈልም የተመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ መኾኑን አሠልጣኝ አማረ በማሳያነት አንስቷል።
የጉና አትሌቲክስ ክለብ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጥላሁን አማረ በበኩሉ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ውላቸውን በጨረሱ አትሌቶች አዳዲሶችን ለመተካት፣ በዕቅድ ለመምራት፣ በአካል ተገኝቶ ለማወያየትና ለመሥራት አለመቻላቸውን አንስተዋል።በመኾኑም የጸጥታ ችግር የክልሉን አትሌቲክስ ምን ያህል እየጎዳው እንደኾነ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዘላለም መልካሙ (ዶ.ር) ከዚህ በፊት የክልሉን አትሌቲክስ ስፖርት ለማሳደግ በሥልጠና ማዕከላት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው የሚል ሀሳብ አንስተው ነበር። ፕሬዝዳንቱ በብሔራዊ ፌዴሬሽን የሚደገፉ ስምንት የሥልጠና ጣቢያዎች፣ በክልሉ የሚታገዙ 16 የሥልጠና ማዕከላት እንዲሁም በዞኖች እና ወረዳዎች የሚደገፉ 126 የሥልጠና ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!