ባሕር ዳር: የካቲት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ላለፉት ሦስት ቀናት በእንግሊዝ ግላስጎ ሲካሄድ በነበረው የ19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከ130 በላይ ሀገሮች የተውጣጡ ከ650 በላይ አትሌቶች ተሳትፈውበታል።
ኢትዮጵያ በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር እና በ3000 ሜትር በሴት እና በወንድ በአጠቃላይ በ8 ሴቶች እና በ5 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች እንደተሳተፈች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሳውቋል፡፡
በሻምፒዮናው በሴቶች 800 ሜትር ፅጌ ዱጉማ እና በሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ኃይሉ የወርቅ፣ በሴቶች 3000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የብር እንዲሁም በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የነሃስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኙ አትሌቶች ሆነዋል።
በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ አንድ ብር በአንድ ነሃስ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎች በማግኘት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሳለች።
በውድድሩ 27 ሀገራት የሜዳልያ ሰንጠረዡ ውስጥ መካተት ችለዋል። አሜሪካ በአጠቃላይ በ20 ሜዳሊያዎች በበላይነት ስታጠናቅቅ ቤልጂየም፣ ኒው ዚላንድ እና ኔዘርላንድስ ተከታዮቹን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!