ኢትዮጵያ መድን ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ ከባሕር ዳር ከተማ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል።

0
247

ባሕር ዳር: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ በ16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቀን 10 ሰዓት ላይ ባሕር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ይጫወታሉ።
ጨዋታውም በቅርቡ የእድሳት ሥራው በተጠናቀቀው ድሬዳዋ ስታዲየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ አክስዮን ማኀበር በድረ ገጹ አስነብቧል።

ባሕር ዳር ከተማ በፕሪሜየር ሊጉ 15 ጨዋታዎችን አድርጓል። በስድስት ጨዋታዎች አሸንፎ በአራቱ አቻ ወጥቶ፣ በአምስቱ ተሸንፎ ፣ በሁለት ንጹህ የግብ ክፍያ በ22 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ከስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ አሸንፎ ወደ ውጤት ተመልሷል።የጣና ሞገዶቹ ከሌሎች ቡድኖች በተለየ ኹኔታ በተጫዋቾች ዝውውር ወቅት በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። በመኾኑም ሦስት አጥቂዎችን ከሰሞኑ አስፈርመዋልና ነው።

በአዲስ የተቀላቀሉት ተጫዋቾች በቡድኑ ውጤት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣሉም ተብሎ ይጠበቃል።በባሕር ዳር ከተማዎች በኩል አጥቂው ሱሌይማን ትራኦሬ ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋች ነው።

ኢትዮጵያ መድንም እንደ ባሕር ዳር ከተማ ኹሉ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ በሁለቱ ብቻ አሸንፏል። በስድስት ጨዋታዎች፣ አቻ ወጥቷል፣ በሰባቱ ደግሞ ተሸንፏል። በ10 የግብ እዳ እና በ12 ነጥብ ደረጃው 13ኛ ነው። ስለኾነም ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ መድን በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ጥሩ የማሸነፍ ሥነ-ልቦና ተጫውቷል። መድን ያለበትን ክፍተት ለመሙላትም በአጋማሹ የዝውውር ወቅት ሚሊዮን ሰለሞን እና አናንያ ጌታቸውን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

ይሁን እና የተጫዋቾች የዝውውር ሂደት ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ የዛሬው ጨዋታ ያልፋቸዋል ነው የተባለው። ንጋቱ ገብረስላሴ ደግሞ በጉዳት እንደማይሰለፍ ታውቋል።
ምሽት 1 ሰዓት ደግሞ ሀምበሪቾዎች ከድሬዳዋ ከተማ እንደሚጫወቱ ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here