ባሕርዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኡጋንዳ ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ በ2027 የሚደረገውን 36ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በጣምራ እንዲያስተናግዱ መመረጣቸው ይታወሳል።ይህን ተከትሎ ኡጋንዳ አዳዲስ ስታዲየሞችን እየገነባች ነው። የነባሮችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ መጀመሯን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዮዎሪ ሙሴቬኒ አስታውቀዋል።
ሙሴቬኒ በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አዲስ ስታዲየም በሚገነባበት የሆይማ ከተማ የቦታ መረጣ እና የተቋራጭ ልየታ ተደርጎ መጠናቀቁን ተናግረዋል። ስታዲየሙ ሁለገብ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ይገነባል ነው የተባለው።
ሌላኛው በአዲስ እየተሠራ ያለው የናኪቩቦ ስታዲየም ነው። ይህ ስታዲየም 20 ሺህ ተመልካቾችን እንዲይዝ ኾኖ የተገነባ ቢኾንም አሁን ወደ 45 ሺህ መቀመጫ እንዲኖረው እየተሠራ ይገኛል።
የናኪቩቦ ስታዲየም ከእግር ኳስ በተጨማሪ የእጅ፣ የመረብ እና የቅርጫት ኳስ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ ተደርጎ ነው እየተገነባ የሚገኘው። በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይም ለውድድር ዝግጁ እንደሚኾን ተስፋ ተደርጓል። የ2027ቱን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያስተናግዱ ከተመረጡት አንዱ የናኪቩቦ ስታዲየምም ነው።
ሌላው ኡጋንዳ ካላት ምርጥ እና ዘመናዊ ስታዲየም አንዱ “የማንዴላ ብሔራዊ ስታዲየም ” ነው። እንደ ዥንዋ ዘገባ 45 ሺህ 2 መቶ ሁለት መቀመጫዎች ያሉትን ስታዲየም የገነቡት ቻይናውያን ናቸው። “ከቻይና ለኡጋንዳ ” የተሰጠ መኾኑንም ዘገባው አስታውሷል።
ስታዲየሞቹ ለኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርብ በመኾናቸው በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ተመራጭ መኾናቸው ተጠቅሷል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!