66 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና ከብዙ ተሳትፏቸው ያላተረፉ ሀገራት

0
28
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
እስካሁን በተካሄዱት 22 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች በበርካታ ጊዜ ተሳትፎ ተጠቃሚ የኾኑ ሀገራት አሉ፡፡ በዚህ ረገድ በ22ቱም ውድድሮች በመሳተፍ ብቸኛዋ ሀገር የኾነችው ብራዚል አምስት ጊዜ ሻምፒዮን በመኾን በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡
ከብራዚል በመቀጠል በ21 ውድድሮች የተሳተፈችው ጀርመን አራት ጊዜ ዋንጫውን ስታነሳ ጣሊያን ከ18 ጊዜ ተሳትፎ አራት ጊዜ፣ አርጀንቲና ደግሞ ከ18 ጊዜ ተሳትፎ ሦሥት ጊዜ አሸናፊ ኾነዋል፡፡
ኾኖም ከበርካታ ጊዜያት ተሳትፎ ተጠቃሚ ያልኾኑ ሀገራትም አሉ፡፡ የውድድሩ ታሪክ እንደሚያስረዳው ከ1930ው የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ 10 ሀገራት ብቻ ቢያንስ 15 ጊዜ እና ከዛ በላይ ተሳትፎ አላቸው፡፡
ከእነዚህም መካከል አንድም ጊዜ ለዋንጫ ያልታደሉት ግን ሜክሲኮ እና ቤልጅየም ብቻ ኾነዋል፡፡ሜክሲኮ በ18 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች፡፡ ከፍተኛ የሚባለው ውጤቷ ግን በ1970 እና 1986 ራሷ ባስተናገደቻቸው ውድድሮች እስከ ሩብ ፍጻሜ የተጓዘችበት ነው፡፡
ከዛሬ 96 ዓመት በፊት በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ መሳተፍ ከጀመሩ ሀገራት አንዷ የኾነችው ቤልጅየም በ15 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ቀርባለች፡፡ ተሳትፎዋ ግም ዋንጫ አላመጣም። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙ እየተጠበቀ አልሳካለት ያለው ወርቃማ የእግር ኳስ ትውልዷ ሀገሪቱን ከዋንጫ ጋር ሊያስታርቃት አልቻለም፡፡
የቤልጅየም ከፍተኛው ውጤት በ2018 የሩሲያው ዓለም ዋንጫ 3ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው፡፡
ከሜክሲኮ እና ቤልጅየም የተለየው ግን የስኮትላንድ ኾኗል፡፡
ስኮትላንድ እስካሁን በዘጠኝ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ተሳትፋለች፡፡ ይሁን እና አንድም ጊዜ ከምድብ መርሐ ግብር ተሻግራ አታውቅም፡፡
ያሁ ስፖርት እንደዘገበው ስኮትላንድ በዘጠኝ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ 23 ጨዋታዎችን አድርጋ ማሸነፍ የቻለችው አራቱን ብቻ ነው፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here