71 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና የአዳዲስ ሀገራት ስኬት

0
4
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ባደገበት የ2026 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ቀሪ የማጣሪያ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተጠናቅቀው 48ቱ ተሳታፊ ሀገራት ታውቀዋል፡፡
እ.አ.አ ከ1930 ጀምሮ በየአራት ዓመቱ እየተካሄደ ባለው በዚሁ የዓለም ዋንጫ ውድድር እስካለፈው የ2022ቱ መድረክ ድረስ በድምሩ 80 ሀገራት ተሳታፊ ኾነዋል፡፡
በዘንድሮው እና ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት በሚሳተፉበት ውድድር ደግሞ አራት ሀገራት የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን ያደርጋሉ፡፡ እነዚሁ ሀገራት ኬፕ ቨርዲ፣ ኩራካኦ፣ ኡዝቤኪስታን እና ጆርዳን ናቸው፡፡
እስካሁን በተካሄዱት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊዎች የታዩት በ2006ቱ መድረክ ነበር፡፡ ጀርመን ባስተናገደችው በዚያ ውድድር ስድስት ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፈዋል።
በዚያ ጊዜ የአፍሪካዎቹ አንጎላ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና እና ቶጎን ጨምሮ ዩክሬን እና ትሪንዳድና ቶቤጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ተከስተዋል፡፡
የዓለም ዋንጫው ዘመናዊ ዘመን መባቻ ተደርጎ ከሚወሰደው የ1950ው ውድድር ጀምሮ እስካሁን ያለውን አሐዛዊ መረጃ ስናይ በድምሩ 57 ሀገራት የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን አድርገዋል፡፡
ከምድቡ መርሐ ግብር ማለፍ የቻሉት ግን 12ቱ ብቻ ኾነዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰሜን አየርላንድ እና ዌልስ (1958)፤ ዴንማርክ (1986)፤ ኮስታሪካ(1990)፤ ናይጀሪያ እና ሳዑዲ አረቢያ (1994) ፣ ጋና(2006) የምድብ ማጣሪያውን አልፈው እስከ ጥሎ ማለፍ ተጉዘዋል፡፡
አየርላንድ ሪፖብሊክ (1990)፤ ሴኔጋል (2002) እና ዩክሬን (2006) ደግሞ ከምድብም አልፎ የጥሎ ማለፍ ዙር ጨዋታዎችን አሸንፈው እስከ ሩብ ፍጻሜ ደርሰዋል፡፡
የፖርቹጋል እና ክሮሺያ ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ኾኖ እናገኛቸዋለን፡፡ ሁለቱ ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት የዓለም ዋንጫ ፖርቹጋል በ1966፤ ክሮሺያ ደግሞ በ1998 ሳይጠበቁ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ተጉዘው ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የእግር ኳሱን ዓለም አስደምመውታል ሲል ያሆ ስፖርትስ አስነብቧል።
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here