ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሀገራት የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ።
16 የአውሮፓ ሀገራት በ2026 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመኾን ዛሬ ፉክክራቸውን ይጀምራሉ። ዛሬ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሀገራት በምድብ ጨዋታዎች በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ማለፍ ያልቻሉት ናቸው። በምድብ ጨዋታዎች በቀጥታ ማለፍ ያልቻሉት ሀገራት በጥሎ ማለፍ ይጫወታሉ። በጥሎ ማለፍ ድል የቀናቸው አራት ሀገራት ደግሞ ወደ ዓለም ዋንጫው ያቀናሉ።
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጣሊያን አንደኛዋ ናት።
ጣሊያን በዓለም ዋንጫ ታሪክ ታላቅ ስም አላት። ይህች በዓለም እግር ኳስ ታላቅ ስም ያላት ሀገር ከዓመታት ወዲህ ከደመቀችበት የዓለም ዋንጫ ርቃለች። ጣሊያን በ2014 የብራዚል የዓለም ዋንጫ ላይ ከተሳተፈች በኋላ ከዓለም ዋንጫ ውድድሮች ርቃለች። ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ደግሞ የጥሎ ማለፍ ጨዋታን ታካሂዳለች።
ዛሬ ምሽት ከሰሜን አየርላንድ ጋር ጨዋታዋን ታካሂዳለች። ጨዋታው ምሽት 4:45 ላይ ይካሄዳል። ጣሊያን በታሪክ ከደመቀችበት ነገር ግን ከዓመታት በኋላ ደግሞ ከከፍታዋ ወርዳ ከራቀችበት የዓለም ዋንጫ ትሳተፍ ይኾን ? የሚለው በጉጉት ይጠበቃል።
በሌሎች ጨዋታዎች ዩክሬን ከስዊድን፣ ዌልስ ከቦሲናያና ኤርዜጎቪና፣ ዴንማርክ ከሰሜን መቄዶኒያ፣ ፖላንድ ከአልቤኒያ፣ ስሎቫኪያ ከኮሶቮ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ከአየርላንድ ጋር ይጫወታሉ። ጨዋታው በተመሳሳይ ሰዓት ምሽት 4:45 ላይ ይካሄዳል።
የቱርክዬ እና የሮማንያ ጨዋታ ደግሞ ምሽት 2:00 ላይ ይካሄዳል። አራት ሀገራት ብቻ ወደ ዓለም ዋንጫ በሚያልፉበት የአውሮፓ ሀገራት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን



