ጥበበኛው ኮከብ

0
34
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እግር ኳስን በላቀ ብቃት ተጫውቷል፤ በታላላቅ ጨዋታዎች ላይ በልዩነት ጎልቶ ታይቷል።
ተዝናንቶ የሚጫወት፤ ሜዳ ላይ የሚደንስ፤ ፈገግታው፣ የእግር ኳስ ችሎታው፤ የደስታ አገላለጹ እና የኳስ አያያዙ የሚናፈቅ ኮከብ ነው።
በታላላቅ ጨዋታዎች፤ በታላላቅ ስታዲየሞች፤ በሚያስፈሩ ደጋፊዎች ፊት በችሎታው ቦርቋል፤ በጥበቡ አስገርሟል። እርሱ አሠልጣኞች የሚወዱት፤ ደጋፊዎች የሚናፍቁት እና የሚሳሱለት ባለ ድንቅ ተሰጥኦ ተጨዋች ነው።
ፈገግታው እና የእግር ኳስ ብቃቱ ሳይለያዩበት፤ ተወዳጅነቱ እና ስብዕናው ሳይከዱት፤ ቄንጠኝነቱ እና አስገራሚነቱ ሳይርቁት ለዓመታት በከፍታ ታይቷል፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ደጋፊዎችን ቀልብ ገዝቷል አንቶኒ ግሪዝማን።
የትውልድ ዘመኑ እ.አ.አ በመጋቢት 21/1991 ነው። የትውልድ ሥፍራው ደግሞ ፈረንሳይ ማኮን በተሰኘች ትንሽዬ መንደር ነው። በዚህች መንደር ኳስን መጫወት የጀመረው ግሪዝማን ከትንሽ መንደር ተነስቶ በዓለም ላይ ትልቅ ስም ገንብቷል። በልጅነቱ ማኮን ለተባለው የአካባቢው የእግር ኳስ ክለብ እየተጫወተ በሌሎች እግር ኳስ ክለቦች ለመጫወት ይሞክር ነበር።
ሰክሰስ ስቶሪ ዶት ኮም ስለ ግሪዝማን ሲጽፍ ለማኮን እየተጫወተ በሌሎች ክልቦችም ዕድሎችን ሞክሯል። ነገር ግን ተቀባይነት አላገኘም ነበር ይላል። ምክንያቱ ደግሞ በአካል ብቃቱ ዳካማነት እና በክብደቱ ዝቅተኛ መኾን ነበር። ተሰጥኦ ያለውን ነገር ግን ቀጫጫውን ኮኮብ አምኖ ዕድለ የሚወሰጠው ክለብ አልነበረም።
ግሪዝማን ግን በቀጫጫ ተክለ ቁማናው ተስፋ ሳይቆርጥ ጠንክሮ መሥራት ቀጠለ። በጠንካራ ሥራው በሞንትፖሊየር እግር ኳስ ክለብ የሙከራ ዕድል ተሰጠው። እ.አ.አ.በ2005 ግሪዝማን በሞንትፖሊየር እግር ኳስ ክለብ በሙከራ ላይ እያለ ከፓሪስ ሴንት ጀርመን አካዳሚ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ተጫወተ። በዚህ ጨዋታ አስደናቂ ብቃት ያሳየው ቀጫጫው ታዳጊ ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ የእግር ኳስ መልማዮችን አስደመመ። የእግር ኳስ ሕይወቱን የሚቀየር የታሪክ ምዕራፍም ኾነው።
የቀጫጫውን ጥበበኛ የተመለከተው የስፔኑ ክለብ ሪያል ሶሲዳድ አስፈረመው። በሪያል ሶሲዳድ ታዳጊዎች ቡድን እየተጫወተ በአቅራቢያው በሚገኝ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ይከታተል ነበር።
በሪያል ሶሲዳድ ለስፔን እግር ኳስ የተዋወቀው ግሪዝማን ባሳየው ብቃት የታላላቆችን ክለቦች ቀልብ ገዛ። እ.አ.አ በ2014 ከሪያል ሶሲዳድ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ አቀና። ከዚያ በኋላ ፈረንሳዊው ኮከብ በዓለም እግር ኳስ ላይ ማብራት ጀመረ። የከዋክብት መናኽሪያ በኾነው የስፔን ላሊጋ ውስጥ የግሪዝማን ስምም ከፍ ብሎ መጠራት ጀመረ። ግሪዝማን በአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ዘልቆ ገባ። የስፔን ስታዲየሞችን በብቃት ደነሰባቸው፤ ግብ እያስቆጠረ ቦረቀባቸው።
በአትሌቲኮ ማድሪድ የደመቀው ግሪዝማን ረብጣ ገንዘብ ተከፍሎበት እ.አ.አ በ2019 ወደ ባርሴሎና ተዛወረ። ነገር ግን በአትሌቲኮ ማድሪድ የታየው ኮከብ በባርሴሎና አልታየም። በባርሴሎና በወትሮ ብቃቱ ያልተገኘው ግሪዝማን ወደ ቀድሞ ቤቱ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ተመለሰ። በዚያም የቀደመ ብቃቱን አገኘ።
ግሪዝማን በክለብ ብቻ ሳይኾን በሀገሩ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንም መድመቅ ጀመረ። ሀገሩን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ወክሎ ተጫውቷል። የዓለም ዋንጫን እስከማሸነፍ የደረሰ የብሔራዊ ቡድን ስኬትም አለው።
ቢቢሲ በዘገባው ግሪዝማን ባለው ተሰጥኦ እና ብቃት ልክ አልተዘመረለትም ይላል። በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች፣ የተለያዩ ኀላፊነቶችን ተሸክሞ የሚገባው ግሪዝማን በአንድ ሥፍራ ብቻ ነጥሮ እንዳይወጣ አድርጎታል ነው የሚለው።
በአትሌቲኮ ማድሪዱ አሠልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ የሚወደደው ግሪዝማን ከእርሳቸው ዘንድ ብዙ ጊዜ ሲደነቅ ኖሯል።
ግሪዝማን ብዙ አለው፤ ጨዋታውን የሚያነብ ብልሃተኛ፣ ደከመኝ የማይል ታታሪ ሠራተኛ፤ አድርግ የሚሉትን ሁሉ የሚያደርግ ለክለቡ ብዙ ሚናዎችን የሚወጣ ነው ይሉታል።
አሁን ይህ ኮከብ ከደመቀበት ሀገር ከስፔን፤ ከደቀመበት ሊግ ከስፔን ላሊጋ፤ ለዓለም ከፍ ብሎ ከታየበት ከአትሌቲኮ ማድሪድ ሊለቅ ነው። የ35 ዓመቱ ኮከብ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አትሌቲኮን ለቅቆ ወደ አሜሪካ ሜጄር ሊግ ሶከር ኦርላንዶ ሲቲ ያመራል።
ግሪዝማን በአትሌቲኮ ማድሪድ የማይረሳ ታሪክ ያለው ኮከብ ነው። ነገር ግን አሁን ከሚወደው እና ከሚወደድበት ክለብ የመልቀቂያ ጊዜው ደርሷል። እርሱም ወደ ኦርላንዶ ሲቲ ያደረገውን ስምምነት አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት የቀጣዩን የሙያ ምዕራፍ ለመጀመር በጣም ጓጉቻለሁ ብሏል። ኦርላንዶን አዲሱ ቤቴ ለማድረግ በጉጉት እጠብቃለሁ ነው ያለው።
እ.አ.አ በ2024 ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለው ግሪዝማን ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በ137 ጨዋታዎች 44 ግቦችን ማስቆጠሩን ቢቢሲ ዘግቧል። ፈረንሳይ በ2018 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እንድትኾን ትልቅ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ነበር።
በአትሌትኮ ማድሪድ ባለታሪክ የኾነው ግሪዝማን በዓመቱ መጨረሻ ክለቡን እንደሚለቅ ባሳወቀበት መልዕክቱ የሚሰማኝን ስሜት በቃላት መግለጽ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ ክለብ ቤቴ ነው፤ እናንተም ቤተሰቤ ናችሁ ብሏል። በአትሌቲኮ ማድሪድ ቤት አስደናቂ ዓመታትን እንዳሳለፈም ገልጿል። የማይረሱ ጨዋታዎች፤ ድሎች እና ደስታዎች እንደነበሩት አንስቷል።
አሁንም ይሄን መለያ ለብሼ የምጫወትባቸው ወራቶች ቀርተውኛል ያለው ግሪዝማን ያለውን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ መኾኑን ተናግሯል። አሁን ጥበበኛው ኮከብ ከአውሮፓ እግር ኳስ የሚርቅበት ጊዜ ቀርቧል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here