“የፋሲል ከነማን ዘላቂ ስኬት ለማረጋገጥ ተቋማዊ ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል” አቶ ቻላቸው ዳኘው

0
28

 

ጎንደር: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል ከነማ ስፖርት ቡድን ሦሥተኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዷል።

ክለቡ ጉባኤውን በጎንደር ከተማ ያካሄደ ሲኾን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የኦዲት ሪፖርትን ለውይይት መነሻ አቅርቧል።

ክለቡ 220 ስፖርተኞችን በሁለቱም ጾታ በእግር ኳስ፣ በእጅ እና በቅርጫት ኳስ እንዲሁም በቦክስ የስፖርት ዓይነቶች አቅፎ ሢሠራ መቆየቱ ተጠቅሷል። ክለቡ ከአጋር አካላት ጋር በመሥራት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የስፖርት ትጥቅ ማሟላቱም ተነግሯል።

በኦዲት ሪፖርቱም 135 ሚሊዮን 346 ሺህ 516 ብር ክለቡ ገቢ ማድረጉ እና 134 ሚሊዮን 266 ሺህ 751 ብር ወጭ እንደተደረገ ተመላክቷል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች የፋሲለደስ ስታዲየምን ዕድሳት በማከናወን ክለቡን ወደ ሜዳው መመለስ እንደሚገባ አንስተዋል። ክለቡን በገንዘብ የማጠናከር ሥራ ማከናዎን እንደሚያስፈልግ ያነሱት ተሳታፊዎቹ ከአሁን በፊት ለክለቡ ቃል የተገባን ገንዘብ ተከታትሎ ማስፈጸም እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ሥራ አሥኪያጅ አብዮት ብርሃኑ ክለቡን ለማጠናከር አዳዲስ አጋሮችን የማፍራት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ እና የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት የማርያም ካሳሁን ክለቡን በሁሉም ዘርፍ ለማሳደግ ተደጋግፎ መሥራትን የሚጠይቅ መኾኑን አስረድተዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው የክለቡን ወጥነት ለማጠናከር ተቋማዊ ግንባታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘውን የፋሲለደስ ስታዲየምን እድሳት ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም አሳውቀዋል።

በጉባኤው የተጓደሉ የክለቡን የቦርድ አባላት ለማሟላት በጠቅላላ ጉባኤው ምርጫ የተካሄደ ሲኾን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንም የቦርድ አባልነት ተሰጥቶታል።

ዘጋቢ :- አገኘሁ አበባው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

#እግር_ኳስ #ስፖርት #ጎል #ፋሲል #አትሌቲክስ #አሚኮ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here