82 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና በታሪክ ዕድለኛ መኾን ያልቻሉ ሀገራትን በጨረፍታ።

0
50

 

ባሕርዳር፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ዋንጫ እያንዳንዳቸው አራት አራት ሀገራትን በያዙ ምድቦች ተከፋፍሎ በምድብ ማጣሪያ መካሄድ የሚጀምር ውድድር ነው፡፡ ይህም ቢያንስ ሦሥት የምድብ ጨዋታዎችን ሳያደርግ ከውድድሩ የሚሰናበት ሀገር አይኖርም ማለት ነው፡፡

በምድብ ጨዋታዎች አለመሸነፍ በውድድሩ ለመቆየት መተማመኛ መስሎ ቢታይም ይህ ያልኾነበት አጋጣሚ ግን ተከስቷል፡፡ በእስከዛሬ የዓለም ዋንጫው ታሪክ አራት ሀገራት በሦሥቱም የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይደርስባቸው ተሰናብተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል አህጉረ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን አንዷ ናት፡፡ የማይበገሩት አናብስት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ በተሳተፉበት የ1982ቱ መድረክ በምድብ ማጣሪያው የውድድሩ ሻምፒዮን ከኾነችው ጣሊያን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ጨምሮ በሦሥቱም ጨዋታዎች ሳይሸነፉ አቻ ነበር የተለያዩት፡፡

ኾኖም አለመሸነፍ ብቻውን በውድድሩ ሊያቆያቸው አልቻለም፡፡ በሦሥቱ ጨዋታዎች አቻ ሲወጡ ያስቆጠሩት ግብ አንድ ብቻ መኾን ገና በጊዜ ወደ ሀገራቸው እንዲሸኙ አድርጓቸዋል፡፡

በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ቤልጂየም እና በ2010ሩ ውድድር ኒውዚላንድም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱም ሀገራት በሦሥት የምድብ ጨዋታዎች አቻ ቢለያዩም በሌሎች የምድቦቻቸው ሀገራት ተበልጠው ተሰናብተዋል፡፡

ከሁሉም የተለየው ግን የስኮትላንድ ነው፡፡ ስኮትላንድ በ1974ቱ የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታዋን አሸንፋ ቀሪዎቹን ሁለት የምድብ ጨዋታዎች አቻ ነበር የተለያየችው፡፡

የያዘችው አምስት ነጥብ ግን በውድድሩ ሊያቆያት አልቻለም፡፡ ከብራዚል እና ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጋር እኩል ነጥብ ኖሯት ነገር ግን ዝቅተኛ የግብ ክፍያ ይዛ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡

አሁን የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራትን ይዞ ነው የሚካሄደው፡፡16 ሀገራት ብቻ በምድብ ማጣሪያ ተሰናብተው 32ቱ ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያልፋሉ፡፡

እንደ እስካሁኑ ከየምድቡ የሚያልፉት ሀገራት ሁለት ብቻ ሳይኾኑ ጥሩ ሦሥተኛ ኾነው የሚያጠናቅቁ ተጨማሪ ስምንት ቡድኖችም ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉ በመኾናቸው ለበርካታ ሀገራት በውድድሩ የመቆየት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ይመስላል፡፡

ዘጋቢ፦ ኃይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here