83 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና ቀይ ካርድ

0
47
ባሕርዳር፡ መጋቢት 11/2018ዓ.ም (አሚኮ)
እ.አ.አ በ1930 በተጀመረው የዓለም እግር እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የተለያዩ ሕግጋት በየጊዜው እየተጨመሩ እና እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለጥፋት የሚሰጡ የቢጫ እና የቀይ ካርዶች ይገኙበታል፡፡
በዓለም ዋንጫው የቢጫ እና ቀይ ካርዶች ተግባራዊ መደረግ የጀመሩት ከ1970ው የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ነበር፡፡አስገራሚው ነገር ግን በዚያ የዓለም ዋንጫ አንድም ቀይ ካርድ አለመታየቱ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ባለው የውድድሩ ታሪክ ከአንድ በላይ የቀይ ካርድ የተመዘዘባቸው ተጫዋቾች እምብዛም አይደሉም፡፡ በዓለም ዋንጫ በተለያየ ጊዜ የተጫወቱ ተጫዋቾች አንድ ጊዜ የቀይ ካርድ አይተው ሊኾን ይችላል።
ነገር ግን በዓለም ዋንጫ ታሪክ እስካሁን ሁለት ቀይ ካርድ ያዩ ተጫዋቾች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ደግሞ ሪጎበርት ሶንግ ነው፡፡
ካሜሩናዊው ተከላካይ ሀገሩን ወክሎ በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሰልፏል፡፡ኾኖም በ17 ዓመት ዕድሜው ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት የ1994ቱ የዓለም ዋንጫ በብራዚሉ ቤቤቶ ላይ በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ በተካሄደው ውድድር ደግሞ በቺሊው ማርሴሎ ሳላስ ላይ ጥፋት ሠርቶ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ በዓለም ዋንጫው ታሪክ ሁለት የቀይ ካርዶች የተመዘዙበት የመጀመሪያው ተጫዋች ኾኗል፡፡
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ፈረንሳዊው ዚነዲን ዚዳን ነው፡፡ ታላቁ የኳስ ጥበበኛ በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ሪጎበርት ሶንግ ሁለተኛ የቀይ ካርዱን ከማየቱ አምስት ቀናት በፊት ነበር በሳዑዲ አረቢያው ፉአድ አሚን ላይ በሠራው አደገኛ ጥፋት የመጀመሪያ ቀይ ካርዱን ያየው፡፡
የዚነዲን ዚዳን ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ቀይ ካርድ ግን በአይረሴነቱ ዛሬ ድረስ ይታወሳል፡፡በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ የደረሱት ፈረንሳይ እና ጣሊያን መደበኛውን 90 ደቂቃ ክፍለ ጊዜ አቻ ተለያይተው ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃዎች አምርተው ነበር፡፡
110ኛው ደቂቃ ላይ ግን አይረሴው ክስተት ተከሰተ፡፡ምን እንደተናገረው እስካሁን ማንም እርግጠኛ ባልኾነበት ቅጽበት ፈረንሳዊው ዚነዲን ዚዳን የጣሊያኑን ተከላካይ ማርኮ ማቴራዚኒን ደረት በቴስታ ደልቆ ከሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ቀይ ካርዱ ጋር ከሜዳ ተሰናበተ፡፡
ሀገሩም በጣሊያን በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፋ ዋንጫውን አጣች፡፡ 2012 ላይ ይህንኑ ክስተት የሚያሳይ 4 ነጥብ 8 ሜትር ርዝመት ያለው ሐውልት ፓሪስ ውስጥ ተሠርቶ አንድ የኳታር ሙዚየም ገዝቶት ዶሃ ውስጥ በሚገኝ የሙዚየሙ ግቢ አቁሞት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ትችቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ሐውልቱ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here