ባሕርዳር፡መጋቢት 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዘንድሮ ይካሄዳል፡፡ የሰሜን አሜሪካዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ የሚያስተናግዱት ይሄው ውድድር ሊጀመር 85 ቀናት ቀርተውታል፡፡
እኛም ይህንኑ የዓለም ዋንጫ መነሻ በማድረግ በውድድሩ ታሪክ የታዩ ክስተቶችን እና አዳዲስ መረጃዎችን በተከታታይ እናጋራችኋለን፡፡ ለዛሬ ደብዛው እንደጠፋ የቀረው የዓለም ዋንጫን ታሪክ እናስታውሳችኋለን።
እ.አ.አ በ1930 የተጀመረው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ታላቅ የውድድር መድረክ ነው፡፡
ውድድሩ ሲጀመር አሸናፊ ለሚኾኑ ሀገራት የሚበረከተው ዋንጫ የዓለም ዋንጫው እንዲጀመር ጉልህ አስተዋጽኦ በነበራቸው ጁሊየስ ሪሜት ስም የተሰየመ ነበር፡፡ ይሄው የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ 35 ሴንቲ ሜትር ርዝመት እና 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ክብደት ኖሮት በወርቅ ከተለበጠ የብር ማዕድን የተሠራ ነበር፡፡
ከውድድሩ የዋንጫ ሕግጋት ውስጥ አንዱ በተከታታይ ሦሥት ጊዜ ያሸነፈች ሀገር ዋንጫውን የግሏ አድርጋ ታስቀራለች የሚል ነው፡፡ ይህንን ያሳካች የመጀመሪያዋ እና ብቸኛዋ ሀገር ደግሞ ብራዚል ናት፡፡
ብራዚል 1970 ላይ ነበር ለሦሥተኛ ተከታታይ ጊዜ ሻምፒዮን በመኾን ዋንጫውን የግሏ ያደረገችው፡፡
ይህንን ተከትሎ ፊፋ ከ1974ቱ መድረክ ጀምሮ አዲስ ዋንጫ ለማዘጋጀት ተገድዷል፡፡ ታሪካዊው የብራዚል ዋንጫ ታሪክ ግን በዚህ አላበቃም፡፡በ1983 በሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንዳለ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተሠርቋል፡፡ እስካሁን ድረስም የውኃ ሽታ እንደኾነ ነው፡፡
የመርማሪዎች መላምት ያንን የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የሰረቁት ሌቦች በውስጡ ያለውን ወርቅ ለማግኜት አቅልጠውታል የሚል ነው፡፡ ኾኖም አራት ተጠርጣሪዎች ለእስር ከመዳረጋቸው ውጭ የዘራፊዎቹ ማንነት እስካሁን አይታወቅም፡፡
ብራዚል የግሏ አድርጋው ደብዛው በጠፋው የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ምትክ ከ1974ቱ ውድድር ጀምሮ የተዘጋጀው የፊፋ የዓለም ዋንጫ 36 ነጥብ 8 ሴንቲ ሜትር ርዝመት እና 6 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም ክብደት አለው፡፡ በውስጡ 18 ካራት ወርቅ ይዟል፡፡
ኾኖም ይህንን ዋንጫ አንድም ሀገር የግሉ አድርጎ ማስቀረት አልቻለም፡፡ በርግጥ 5 ጊዜ ሻምፒዮን ከኾነችው ብራዚል ቀጥሎ ጀርመን እና ጣሊያን እያንዳንዳቸው አራት ጊዜ አርጀንቲና ደግሞ ሦሥት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸንፈዋል።
ኾኖም እነዚህ ሀገራት በተከታታይ ሻምፒዮን ስላልኾኑ እና በመካከል ሌሎች ሀገራት ጣልቃ ስለገቡ ዋንጫውን የግላቸው አድርገው ማስቀረት አልቻሉም፡፡
ዘጋቢ፦ ኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



