0
108

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2018 ዓ.ም(አሚኮ) ይህ በዓለም ምርጡ ሊግ ውስጥ የተሠራ አዲስ ታሪክ ነው። ከዚህ ቀደም በእርሱ ዕድሜ ይሄን ያደረገ የለም። ይሄን ያደረገ እርሱ ብቻ ነው። የእርሱ ግብ አሸናፊነትን ያረጋገጠች፣ ነጥብም ያስገኘች ብቻ አይደለችም፤ ታሪክ የሠራች፣ ታሪክ ኾናም የተመዘገበች ናት እንጂ።

ምን አልባትም የዓለም እግር ኳስ አልጋ ወራሽ ይኾናሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ታዳጊዎች መካከል አንደኛው ነው። በእርሱ ዕድሜ የማይጠበቅ ብስለት፣ ብልሃት እና ጥበብ ተችሮታል፤ በእግር ኳስ በቅጡ የሚዝናና፤ በቅጡም የሚያዝናና ባለ አስደናቂ ተሰጥዖ ነው።

የተወለደው እ.አ.አ ታኅሣሥ 2009 በለንደን ሰሜን ምሥራቅ ንፍቅ በምትገኝ ቸልምስፎርድ በተሰኘች ከተማ ነው። ስሙ ማክስ ዳውማን ይባላል። አሁን ላይ ለአርሰናል እየተጫወተ ነው።
ይህች ከተማ የጥንት ታሪክ የሚነገርባት፤ የጥንት ቅርስ እና ጥበብ የያዘች ውብ ሥፍራ ናት። በዚህች ውብ እና ታሪክ የሞላባት ሥፍራ የተገኘው ብላቴና አሁን ላይ ስሙ በዓለም ሚዲያ ላይ ናኝቷል። በእግር ኳስ ላይ በሠራው ታሪክ ስሙን የዓለም ሚዲያዎች እያነሱ እያሞገሱት ነው።

ወደ ዋና ከተማ ክለብ አርሰናል የመጣው ገና በለጋ ዕድሜው ነው። በየዕድሜ እርከኑ በሚገኙ የአርሰናል አካዳሚዎች የማይታመኑ የሚመስሉ ተሰጥዖዎችን ያሳየው ታዳጊው ለዓለም እግር ኳስ የተዋወቀው በለጋ ዕድሜው ነው።

በ14 ዓመቱ ከአርሰናል ዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እንዲሠራ የተፈቀደለት ማክስ ዳውማን ጅማሮው ያማረው በማለዳው ነው። ስካይ ስፖርት በዘገባው ምን አልባትም ሚኬል አርቴታ ባይኾኑ ኖሮ ይሄ ልጅ ወደ ዋናው ቡድን በዚህ ዕድሜ እና ፍጥነት አይመጣም ነበር ይላል። አሁን ላይ በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ በጣም የተወራለት ታዳጊ ነው የሚለው ዘገባው ሁሉም ዓይነት ችሎታ አለው፤ አስተሳሰቡ የላቀ ነው፤ ከእንግዲህ የማክስ ዶውማን ዕድገት ቀጣይነት አለው ነው የሚለው።

የአርሰናል አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ እርሱ በልምምድ ወቅት የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች የማይታመኑ ናቸው በማለት አወድሰውታል። የአርሰናሉ አማካይ ዴክላን ራይስ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ምርጥ ልጅ ብሎታል።

ቢቢሲ በዘገባው ማክስ ዳውማን በአርሰናል ቤት ክብረ ወሰኖችን እየሰበረ ነው ብሏል። በትንሽ ዕድሜው በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኤፍኤ ዋንጫ የተጫወተ የአርሰናል ተጫዋቾች ተብሎ ስሙ የተመዘገበው ይህ ታዳጊ ትናንት ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋቾች በመባል አዲስ ታሪክ ሠርቷል። ትናንት ምሽት አርሰናል ኤቨርተንን 2ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው ዳውማን ግቧ ስሙን በአዲስ የታሪክ መዝገብ ላይ አስፍራለታለች።

የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ኢሲያ ከተጓዘው የአርሰናል ቡድን ጋር አብሮ የተጓዘው ማክስ ዳውማን አብረው ከተጓዙ ታዳጊዎች መካከል አደገኛው እርሱ ነበር ይላል ቢቢሲ በዘገባው።

በቅድመ ውድድር ወቅት በተደረጉ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ዳውማን አስደናቂ ተሰጥዖውን አሳየ። ይህን የተመለከቱት አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ አድናቆታቸውን በተደጋጋሚ ቸሩት።

ቢቢሲ ማክስ ዳውማን ታሪክ ስለሠራበት የትናንቱ ጨዋታ ሲጽፍ አርሰናል ከኤቨርተን ጋር ያደረገው ጨዋታ እስከመጨረሻው ደቂቃ ገደማ ድረስ የሚያበሳጭ ይመስል ነበር። አርሰናሎች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያሰፋበትን ዕድል የተነጠቁም ይመስል ነበር።

ይህ ደግሞ ለዋንጫ ቅድመ ግምት ለተሰጠው አርሰናል የሚያበሳጭ ነው። ነገር ግን ሚኬል አርቴታ ቀይረው ያስገቧቸው ሁለት ተጫዋቾች የሚያበሳጭ ኾኖ ሊያልፍ የነበረውን ቀን በደስታ ቀየሩት። በስታዲየሙ የነበረውን የስጋት ድባብ አስደናቂ ወደ ኾነ የደስታ ድባብ መለሱት። ካይ ሀቨርትን አስወጥተው ቪክቶር ዮከሬሽን፤ ማርቲን ዙቢሜንድን አስውጥተው ማክስ ዳውማንን አስገቡ። እነዚህ ተጨዋቾች በአለቀ ደቂቃ ግቦችን አስቆጥረው ስታዲየሙን በደስታ ናጡት።

ዳውማን ግብ ሲያስቆጥር ሜኬር አርቴታን እና የአርሰናል ተጫዋቾች የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል የአንበሳ ደቦል በደስታ ቦረቁ። ዘለሉ።

በ16 ዓመት ከ73ኛ ቀኑ ላይ ግብ ያስቆጠረው ማክስ ዳውማን በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ በዕድሜ ትንሽ ኾኖ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ተብሎ በታሪክ ተመዘገበ።

ከጨዋታው በኋላ ሚኬል አርቴታ ማክስ ዳውማን ግብ ያስቆጠረበትን አጋጣሚ ሲገልጹ አስደናቂ ነበር፤ ሁሉም በደስታ ይዘል ነበር፤ እርሱ ግብ ማስቆጠሩ ብቻ ሳይኾን ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውንም ቀይሮታል አሉ።

ዳውማን ለራሱ ታሪክ ሢሠራ ክለቡን ደግሞ የዋንጫ ግስጋሴውን አሳምሮለታል። አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ በዚህ ዕድሜ ይሄን ማድረግ የተለመደ አይደለም፤ ለእሱ ጫና አይሰማውም ብለዋል። ትናንት በኤምሬትስ ስታዲዬም ዳውማን ታሪክ ሢሠራ የነበሩ ደጋፊዎች የ16 ዓመቱ ታዳጊ ግብ ሲያስቆጥር በስታዲየም ነበርኩ ብለው ታሪክ እንደሚናገሩም አስባለሁ ነው ያሉት ሚኬል አርቴታ።

አሁን ላይ የዓለም ሚዲያዎች የዚህን ታዳጊ ስም እያነሱ እየተነጋገሩ ነው። አርሰናል እ.አ.አ በ2004 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ካሸነፈ ወዲህ የሊጉን ዋንጫ አሸንፎ አያውቅም። አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ካሸነፈ ከዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ2009 የተወለደው ማክስ ዳውማን የአርሰናልን የዋንጫ ግስጋሴ አሳምሮታል።

አርሰናል በዚህ ከቀጠለ ከዓመታት በኋላ የዋንጫ ረሃቡን ያስታግሳል። አርሰናል በዚህ የውድድር ዘመን ለአራት ዋንጫ እየተፎካከረ ነው። ሁሉም ይሳካለት ይኾን? የሚለው በቀሪ ጊዜያት ይጠበቃል። የማክስ ዳውማን ታሪክ ግን ደምቆ ይኖራል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here