ባሕርዳር: የካቲት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረንሳዊ አጥቂ ከኮንትራት ማራዘም ጋር በተያያዘ ከፒስጅ ጋር ውዝግብ ውስጥ ቆይቷል።በቅርቡ ደግሞ በወጭው ክረምት የፈረንሳዩን ክለብ እንደሚለቅ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።ተጫዋቹ ለረያል ማድሪድ ለመጫወት የቆየ ፍላጎት እንዳለው ቢታወቅም ነጮቹን ለመቀላቀሉ ግን እርግጠኛ መኾን አልተቻለም።
ነገር ግን ቢቢሲ ባወጣው መረጃ መሰረት ማድሪድ እና ምባቤ የቆየ መፈላለጋቸውን ወደ ዳር ለማድረስ ጫፍ ደርሰዋል።በዚህ መሰረት ፈረንሳዊ አጥቂ ለአምስት ዓመት በማድሪድ ለመቆየት ፊርማውን ያኖራል። በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ዩሮ የሚከፈለው ሲኾን፣ 150 ሚሊዮን ዩሮ በአምስት ዓመት ቆይታው በተለያየ መንገድ የሚያገኝም ይኾናል።
ክሮሽያዊ ሉካ ሞድሪች በዓመቱ መጨረሻ ማድሪድን የሚለቅ በመኾኑ ምባፔ 10 ቁጥር መለያ እንደሚሰጠውም ታውቋል።
ኪሊያን ምባፔ ከሰባት ዓመታት በፊት ከሞናኮ ፒስጅን መቀላቀሉ ይታወሳል።ለፒስጅም 244 ግቦችን ሲያስቆጥር 93 ኳሶችን ለጓደኞቹ አቀብሎ ጎል ኾነዋል።291 ጊዜ ለክለቡ ተጫውቷል፤ አምስት የሊግ አንድ ዋንጫዎችንም አሳክቷል።
ምባፔ ባለፈው ክረምት ከሳኡዲ አረቢያው አል ሂላል ክለብ የዓለም ክብረወሰን በኾነ ገንዘብ የዝውውር ጥያቄ ቢቀርብለትም ውድቅ አድርጓታል። የክለቡ ባለቤቶች ዝውውሩን እንዲቀበል ወይም ውሉን እንዲያራዝም በመፈለጋቸውም ከተጫዋቹ ጋር አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር ይታወሳል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!