የሁለገቡ የስፖርት ሰው ሕልፈት

0
281

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቴረንስ ፍሬድሪክ ቬናብልስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 6/1943 ኤሴክስ በተባለች ከተማ እንግሊዝ ውስጥ ተወለደ፡፡

ይህ ብላቴና የ13 ዓመት ልጅ ሳለ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመኾን ሻተ፡፡ ይሕም የእግር ኳስ ፍቅር ካላቸው አያቱ ጋር በማደጉ የመጣ ነው፡፡ በመኾኑም ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን እግር ኳስን ሁለተኛ ሥራየ ብሎ ተያያዘው፡፡ ሰርክ አያቱን ጥሩ ተጫዋች መኾን እንዴት እንደሚቻል ይወተውታቸዋል፡፡ እሳቸውም የልጁን የልብ መሻት ተረድተው በንድፈ ሐሳብ ከሚነግሩት ባሻገር የተለያዩ የሥልጠና ሥልቶችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እያመጡ ይሰጡትና ያስረዱት ነበር፡፡

በዚህ መልኩ ያደገው ቬናብልስ በ15 ዓመቱ የቼልሲ ታዳጊ ቡድን የዐይን ማረፊያ ኾነና ቡድኑን ተቀላቀለ፡፡ ብቃቱን አስመሰከረ፡፡ በ202 ጨዋታዎች ተሰልፎም እጹብ ድንቅ ብቃቱን አሳየ፡፡

በየጊዜው በቼልሲ በሚያሳየው የአጨዋወት ጥበብ እና ቡድን የመምራት ብቃቱ የተደመሙት የቶትንሃም የእግር ኳስ ሰዎች ተጫዋቹን በገንዘብ ኃይል አማልለው ለመውሰድ አሰፈሰፉ፡፡ በወቅቱ 80 ሺህ ፓውንድ ለስተርሊንግስ በመፈረሙ ሌሎች ተጫዋቾች ዐይናቸው ቶትንሃም ላይ እንዲያሳርፉ አደረገ፡፡

ቬናብልስ በተሰለፈባቸው 115 ጨዋታዎች የተመልካችን ቀልብ ገዛ፡፡ ይሁንና ከቶትንሃም የቡድን መሪዎች ጋር በአንዳንድ ግላዊ ጉዳዩች ዙሪያ መስማማት አልቻለም፡፡ ስለኾነም “እግር ኳስን ለመጫወት ምቹ ሁኔታዎች ያሥፈልጋሉ” በማለት ቡድኑን ለመልቀቅ ወሰነ፡፡

ኩዊንስ ፓርክ ራንጀርስ ይህን የቬናቤልስ እና የቶትንሃም ቡድን መሪዎችን እሰጥ አገባ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም አሰፈሰፉ፡፡ ጠጋ ብለውም “70 ሺህ ፓውንድ ደመወዝ፣ ቪላ ቤት እና እጅግ ዘመናዊ ላንድ ሮቨር መኪና እንስጥህ” አሉት፡፡ እሱም አላመነታም፡፡

በቃ! ለኩዊንስ ፓርክ ራንጀርስ ፈረመ፡፡ በ177 ጨዋታዎች ተሰልፎም ተጫወተ፡፡ ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ክሪስታል ፓላስ፣ ካንተርበሪ-ማሪክቪል ኦሎምፒክ፣ ካንተርበሪ-ማሪክቪል ኦሎምፒክ እና ቅዱስ ፓትሪክ አትሌቲክ የተጫወተባቸው ቡድኖች ናቸው፡፡

በጠቅላላውም በቡድን ደረጃ በ528 ጨዋታዎች መሰለፍ የቻለ አመለ ሸጋ ተጫዋች እንደኾነ ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድንም በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

ቬናብልስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1976 ፊቱን ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝነት መለሰ። በሦስት ሀገራት ተዘዋውሮ ስድስት ቡድኖችን አሠልጥኗል፡፡
የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን (ሦስቱ አናብስትን) ረዳት አሠልጣኝ በመኾን ብሔራዊ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡

ይህ ሰው፤ ተጫዋች እና አሠልጣኝ ብቻ አልነበረም፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ “ሃዘል” የተባለ የቴሌቪዥን ተከታታይ ልብ ወለድ ድራማ ደራሲም ነበር፡፡ ይህ ሥራውም በቢቢሲ ቴሌቪዥን ተናኘ እና በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ ዕውቅናን አተረፈ፡፡

የኾነ ኾኖ ስመ ጥሩ የስፖርት ሰው በ80 ዓመቱ ማረፉ ተሰምቷል፡፡

ሞቱን ተከትሎም ጋሪ ኔቪል “ኤክስ” በተሰኘው የመረጃ ማሰራጫ አውታር እንዲህ ሲል ጽፏል-“ብሪታንያ የላቀ ተሰጥኦ የነበረውን ሰው አጥታለች “ብሏል ።

ጋሪ ሊነከር በበኩሉ “ተአምኛ፣ጥበበኛ ፣ጠንካራ ተጫዋች እንዲሁም ምርጥ አሠልጣኝ ነበር” ብሎታል፡፡

የአሁኑ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት “ቬናቤልስ የሰዎችን ስሜት በእግር ኳስ መግዛት የቻለ ጎበዝ ሰው ነው እንግሊዝ ያጣችው፤ በቃ ! ሁለገቡን የስፖርት ሰው በክብር እንሸኘዋለን “በማለት ሀዘኑን አስፍሯል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here