ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
በሊጉ ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር ባሻገር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ይዞ ለማጠናቀቅ ብርቱ ፉክክር እየተካሄደ ነው።
ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ማንቸስተር ዩናይትድ እና አስቶን ቪላ ይገናኛሉ። የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ የሚደርገውን ፉክክር ያሳምርለታል።
ጨዋታው በማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ በኦልድትራፎርድ ይካሄዳል። ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ከአስቶንቪላ ጋር ከተጫወተባቸው 37 ጨዋታዎች ውስጥ የተሸነፈው በሁለት ብቻ መኾኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የቀድሞው ታሪካዊ ተጨዋች ማይክል ካሪክ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተረከበ ወዲህ ክለቡ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። የዛሬውን ጨዋታም እንደሚያሸንፍ ቅድመ ግምት አግኝቷል።
ጨዋታው ቀን 11:00 ላይ ይካሄዳል።
ኖቲንግሃም ፎረስት ከፉልሃም፣ ክርስቲያል ፓላስ ከሊድስ ዩናይትድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም በተመሳሳይ 11:00 ላይ ይደረጋሉ።
የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ይዞ ለማጠናቀቅ እየተፎካከረ የሚገኘው ሊቨርፑል ምሽት 1:30 ላይ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር ይጫወታል። ሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ይዞ ለማጠናቀቅ ቶተንሃም ደግሞ ከሊጉ ላለመውረድ የሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር ነው።
በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚጫወተው ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ይጠበቃል። ሊቨርፑል በሜዳው ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የበላይነት እንዳለው ቢቢሲ አስነብቧል።
በደካማ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ያለፉት አምስት ጨዋታዎችን ተሸንፏል።
ቶተንሃም በ2026 አንድም የፕሪሚየር ሊግ ድል የለውም። በዚህ ከቀጠለ ከሊጉ የመትረፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



