አዲስ አበባ: መጋቢት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ የተሰጠው የሴኡል ማራቶን በመጪው እሑድ ይካሄዳል፡፡
በሁለቱም ጾታ ስመ ጥር አትሌቶች የሚፎካከሩበት የ2026 የሴኡል ማራቶን በተለይም በወንዶቹ በኩል ክብረወሰን ሊሰበር እንደሚችል ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች የግል ምርጥ ሰዓት ያላቸው 5 አትሌቶች ይሄንን የማድረግ አቅም እንዳላቸውም የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡
ይሄም ማለት እ.አ.አ 2022 ሞስነት ገረመው 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ካስመዘገበው የቦታው ክብረ ወሰን የተሻለ ሰዓት ያላቸው አትሌቶችን ያሰባሰበ ፉክክርም መኾኑ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ከነዚህም መካከል አራቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
በ2022 ሞስነት ገረመው 2 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ካስመዘገበው የቦታው ክብረ ወሰን በኋላ አምደወርቅ ዋለለኝ፤ ጀማል ይመር እና ሀፍቱ ተክሎ በተከታታይ የሴኡል ማራቶንን ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ቀዳሚ ተፎካካሪ ይኾናሉ ያላቸውን 13 አትሌቶች በግል ፈጣን ሰዓታቸው መሰረት ይፋ ሲያደርግም አምስቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል ባለፈው ዓመት 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ በማስመዝገብ አሸናፊ የኾነው ሀፍቱ ተክሉ ይገኝበታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2023 በርሊን ማራቶን ላይ 5ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ የግሉ ፈጣን ሰዓት ሲኾን ከሴኡል ማራቶን ፈጣን ሰዓትም በ1 ሰከንድ የሚፈጥን ነው፡፡
ሴኡል ለሀፍቱ ልዩ ትርጉም አላት፡፡ አትሌቱ የመጀመሪያ ማራቶን ፉክክሩን የጀመረባት ከተማ ናትና፡፡ እ.አ.አ 2023 የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን አድርጎ በ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት 3ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ጉዞውን ያሳመረባት ከተማ ኾናለች፡፡ በ4 ዓመት ውስጥም ለ2ኛ ጊዜ ለማሸነፍ ጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡ ሌላኛው ተሳታፊ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሳይ ለማ ሲኾን የዓለማችን 4ኛ ፈጣን ሰዓት በእጁ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ በ2023 በቫሌንሲያ ያስመዘገበው 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ሰዓትም ከካልቪን ኪፕቱም፤ ኢሊ ድ
ኪፕቾጌ እና ቀነኒሳ በቀለ በመቀጠል የዓለማችን 4ኛው የማራቶን የሁልጊዜም ፈጣን ሰዓት ኾኗል፡፡
ከዚህም በኋላ ባደረጋቸው የማራቶን ውድድሮች ስኬታማ ባይኾንም ወደ ድል ለመመለስ በመጭው እሑድ ሴኡልን ይጠባበቃል፡፡ ከ2ቱ በተጨማሪ ጌታነህ ሞላ እና ጸጋዬ ጌታቸው ለማሸነፍ ቅድመ ግምት ያገኙ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያውያኖቹ በተጨማሪ ስድስት ኬኒያውያን አትሌቶች ተፎካካሪ ናቸው። ባላቸው ሰዓት መሠረትም ከኢትዮጵያውያን በመቀጠል ሊያሸንፉም ይችላሉ ተብሏል፡፡ የኬኒያ አዲሱ የማራቶን የፊት ገጽ ኾኖ የመጣው ኒክ ኪቱንዱ በቅርቡ በዚሁ በኮሪያ ዋና ከተማ የተካሄደው የጄቲቢሲ ሴኡል ማራቶንን በ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ነበር፡፡
ባለልምዱ ሳሚ ኪትዋራ ሌላኛው ከኬንያ የሚጠበቅ ነው። የቻይናው ኦሊምፒያን እና የኤዥያ ጨዋታዎች ሻምፒዮን ሄጂ ሌላው የሚጠቀስ ተሳታፊ ነው።
በሴቶች ውድድር ደግሞ ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች የሮጡ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከኬኒያዊቷ አትሌት ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል፡፡ ባላቸው ፈጣን ሰዓት መሠረት ጥሩዬ መስፍን እ.አ.አ በ2024 በቫሌንሲያ ሦስተኛ ወጥታ ባስመዘገበችው 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ የግል ምርጥ ሰዓት ዝርዝሩን ትመራለች። በቅርቡ ኅዳር ወር ላይ በሻንግሃይ በተደረገው መድረክ ደግሞ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ደረጃን የያዘች ሲኾን የመጀመሪያ የማራቶን ድሏን ለመቀዳጀት ትጥራለች።
ቦሰና ሙላቴ ከ10 ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ስትኾን በ2024 የበርሊን ማራቶን ሦስተኛ ኾና ያጠናቀቀችበት 2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ 2 የኬኒያ አትሌቶች ተሳታፊ ሲኾኑ ለኢትዮጵያውያኑ ተፎካካሪ ትኾናለች ተብላ የምትጠበቀው ጆይስ ቼፕኬሞይ ቴሌ ናት።
በ2024 በሉብሊያና የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ስታደርግ እስካሁን የተሳተፈችባቸውን ሦስት ማራቶኖች በሉብሊያና፣ በሙምባይ እና በጓንግዡ ማሸነፏ ለኢትዮጵያውያኑ ብርቱ ተፎካካሪ ያደርጋታል፡፡ የሀገሯ ልጅ ሞኒካ ቺቤት እነ የቻይናዋ ውቢንግ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ሀቨን ኃይሉ፣ በቀለች ጉደታ፣ ዝናሽ ሰንበታ፣ አንቺዓለም ሃይማኖት፣ ቤተልሔም አፈንጉስ፣ አይናዲስ ተሾመ፣ ከበቡሽ ይስማ እና መዲና ደሜ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡ አስካሁን በተደረጉት 79 የሴኡል ማራቶን መድረኮች 5 ወንድ እና 8 ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በሐናማርያም መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



