አዲስ አበባ: መጋቢት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሞንዶ ዱፕላንቲስ የዓለም የከፍታ ዝላይ ክብረ ወሰንን ለ15ኛ ጊዜ አሻሽሏል።
ትናንት በኡፕሳላ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር ላይ ሞንዶ 6 ነጥብ 31 ሜትር በመዝለል ከፍ ብሎ አምሽቷል። ይሄም በስፓርቱ በራሱ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን አንድ ሴንቲ ሜትር በመጨመር አሸንፏል።
የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና ባለክብሩ ኮከብ ሞንዶ ዱፕላንቲስ በውድድሩ አንድም ጊዜ ሳይወድቅ አጠናቅቋል። ውድድሩን በ5 ነጥብ 65 ሜትር የጀመረ ሲኾን በመቀጠልም 5 ነጥብ 9 ሜትር እና 6 ነጥብ 08 ሜትርን በመጀመሪያ የዝላይ ሙከራዎቹ አሳክቷል።
ከዚያም በ6 ነጥብ 31 ሜትር ረግቶ የራሱን ክብረወሰን አሻሽሏል። ሞንዶ ዱፕላንቲስ ይሄንን ከፍታ የዘለለው በሀገሩ እና በትውልድ ቦታው ኡፕሳላ መኾኑ ደግሞ ለየት አድርጎታል።
የኖርዌዩ ሶንድሬ ጉቶርምሰን 6 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ወጥቷል። ይህም በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ስድስት ሜትር የዘለለበት ውጤቱ ኾኖ ተመዝግቧል። ለ15ተኛ ጊዜ ክብረወሰንን ያሻሻለው ሞንዶ ዱፕላንቲስ ከእርሱ በቀር ይህን ያደረገ የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ የለም።
ዛካሪ ብራድፎርድ፣ ሳም ኬንድሪክስ እና ኩርቲስ ማርሻል እያንዳንዳቸው 5 ነጥብ 9 ሜትር በመዝለል ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸውን
ከዓለም አትሌቲክስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



