ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም ካየቻቸው ድንቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ከቀዳሚዎቹ አንደኛው ነው። እግርኳስን በጥበብ ተጫውቷል። በዓለም ዙሪያ የሚሊዮኖችን ልብ ገዝቷል። ኳስን በእግር እንደዚህ መጫወት ይቻላል ወይ? እስኪባል ድረስ አስደናቂ ችሎታውን ለዓመታት አሳይቷል።
የዓለም ታላላቅ አሠልጣኝ እኔ ባሠለጠንኩት፣ የዓለም ታላላቅ ክለቦች እኔ ባስፈረምኩት፣ ለእኔ ባጫወትኩት፣ ታላላቅ ተጫዋቾች ከእኔ ጋር በተጫወተ ብለው የሚመኙት ድንቅ ተጫዋች ነው።
በእግርኳስ ይህ ቀረሽ የማይባል ክብርን አሳክቷል። ከሀገር ውስጥ ዋንጫዎች እስከ ዓለም ዋንጫ ድረስ አሸናፊ ነው። በእግርኳስ የተቀዳጃቸው የግል ክብሮችም አያሌ ናቸው ሊዮኔል ሜሲ።
ከደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አርጀንቲና ምድር የተገኘው ይህ ድንቅ ተጫዋች በዓለም እግር ኳስ ገናና ስም ገንብቷል። በሠራው የእግርኳስ ገድል ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል። ሜሲ አብዛኛው የእግርኳስ ሕይወቱን ያሳለፈው እና አስደናቂ ብቃቱን ያሳየው በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ነው። በባርሴሎና ቤት በርካታ ክብሮችን አሳክቷል።
የባርሴሎና የምንግዜውም ባለ ታሪክ የኾነው ይህ ኮከብ ወደ ፈረንሳይ ተሻግሮ ለፒኤስጂም ተጫውቷል። አሁን ደግሞ ወደ አሜሪካ ሜጄር ሊግ ሶከር አቅንቶ ለኢንተር ሚያሚ እየተጫወተ ነው።
ሜሲ ወደ አሜሪካ ካቀናበት ጊዜ ጀምሮ ሚዲያዎች እና የእግር ኳስ ወዳጆች የአሜሪካን እግር ኳስ ለመከታተል ተገድደዋል። ምክንያቱም እርሱ የሚናፈቅ እና ሊያዩት የሚያጓጓ ነውና።
በእግር ኳስ እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ የሌለው ኢንተር ሚያሚም ሊዮኔል ሜሲን ካስፈረመ በኋላ አዳዲስ ክብሮችን እያሳካ ነው። ዋንጫዎችን አሸንፏል። በሜሲ ስም እና ዝና የክለቡ ተከታዮች እና የገቢው መጠንም አድጓል።
ክብሮችን ያሳኩት ሜሲ እና የኢንተር ሚያሚ የቡድን አባላት ትናንት በአሜሪካ በነጩ ቤተ መንግሥት ጉብኝት አድርገዋል። ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ጋርም ተወያይተዋል።
ቢቢሲ በዘገባው ሊዮኔል ሜሲ እና ኢንተር ሚያሚ ከሜጄር ሊግ ሶከር ዋንጫ ድል በኋላ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ጋር በነጩ ቤተ መንግሥት ተገናኝተዋል ብሏል።
የኢንተር ሚያሚ በሜጄር ሊግ ሶከር በዋሽንግተን ዲሲ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ቅዳሜ ይጨዋታል። ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ሜሲ እና የኢንተር ሚያሚ የቡድን አባላት በነጩ ቤተ መንግሥት ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ እንደቀረበላቸው ቢቢሲ አስታውሷል። ግብዣውን ተከትሎ ሚሲ እና የኢንተር ሚያሚ የቡድን አባላት የነጩን ቤተ መንግሥት ጎብኝተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ሜሲ በዓለም ላይ ወደ አለ ወደ የትኛውም ቡድን መሄድ ትችል ነበር። አንተ ኢንተር ማያሚን መርጠሃል። ይህን ስላደረክ ሁላችንም እናመሠግንሃለን ብለውታል። ሜሲ እዚህ እንዲያሸንፍ ስለሚጠበቅ ለማሸነፍ ጫና እንደሚያድርበትም አንስተዋል።
ኢኤስፒኤን በዘገባው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሜጄር ሊግ ሶከር ዋንጫ ያሸነፈው ኢንተር ሚያሚ በነጩ ቤተ መንግሥት አቀባበል ተደርጎለታል ብሏል። የክለቡ አምበል ሜሲ ለፕሬዝዳንት ትራንፕ ስጦታ ማበርከቱንም ገልጿል።
ሐምሌ 2023 ለኢንተር ሚያሚ የፈረመው ሜሲ የምንጊዜውም የእግር ኳስ ተቀናቃኙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በነጩ ቤተ መንግሥት ጉብኝት ካደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የነጩን ቤተ መንግሥት መጎብኘቱንም ኢኤስፒኤን ጽፏል።
የሜጄር ሊግ ሶከር አሸናፊ የኾነው ቡድን የነጩ ቤተ መንግሥትን የመጎብኘት የቆየ ልምድ እና ታሪክ አለ። ዲሲ ዩናይትድ እ.አ.አ በ1998 የሜጄር ሊግ ሶከር አሸናፊ ሲኾን የነጩ ቤተ መንግሥትን የጎበኘ የመጀመሪያው ክለብ እንደኾነ ኢ ኤስ ፒኤን አስታውሷል። ኤል ኤ ጋላክሲ እ.አ.አ በ2011፣ 2012 እና 2014 የሊጉን ዋንጫ በማሸነፍ የነጩን ቤተ መንግሥት ጎብኝቷል።
ትናንት ኢንተር ሚያሚ እና ሜሲ ያደረጉት ጉብኝትም የዚሁ ታሪክ አካል ነው ተብሏል። የሜሲ የነጩ ቤተ መንግሥት ጉብኝት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ከቡድኑ በላይ የሜሲ በነጩ ቤተ መንግሥት መገኘት መነጋገሪያ ጉዳይ ኾኗል።
ለአሜሪካ እግር ኳስ ድምቀት የኾነው ሜሲ በኢንተ ሚያሚ እስከ 2028 የሚያቆየውን ውል መፈረሙ ይታወሳል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



