ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ለማጥበብ የሚያስችለውን ውጤት ለማስመዝገብ ከሜዳው ውጭ ከሴልታ ቪጎ ጋር ምሽት 5:00 ይጫዎታል።
ሪያል ማድሪድ እስካሁን ካደረጋቸው 26 የላሊጋ ጨዋታዎች 60 ነጥብ በመሠብሠብ በሁለተኛነት ተቀምጧል።
ከላ ሊጋው መሪ ባርሴሎና ያለው የነጥብ ልዩነትም አራት ብቻ ነው። ዛሬ ካሸነፈ ባርሴሎና እስኪጫወት ድረስ ልዩነቱን ወደ አንድ ነጥብ ማውረድ ያስችለዋል።
ስፖርትስ ሞል ድረ ገጽ እንዳስነበበው ሪያል ማድሪድ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ይቸገራል። ምክንያቱ ደግሞ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን በጉዳት የማያሰልፍ በመኾኑ ነው ብሏል።
ኤደር ሚሊታዖ፣ ጁድ ቤሊንግሃም፣ ዳኒ ሴባልሎስ፣ ኪሊያን ምባፔ፣ ሮድሪጎ እና ዴቪድ አላባ ባጋጠማቸው ጉዳት ለሪያል ማድሪድ የማይሰለፉ ተጫዋቾች መኾናቸውን ነው ስፖርትስ ሞል የተነተነው።
የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ አልቫሮ አርቤሎአ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት አስተያዬት ከላሊጋው መሪ ባርሴሎና ያለውን የነጥብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ለማድረግ እንጫወታለን ብለዋል። ከባርሴሎና ጋር የዋንጫ ፍልሚያው ይቀጥላል ነው ያሉት።
ተጋጣሚው ሴልታ ቪጎ ከ26 ጨዋታዎች 40 ነጥብ በመያዝ ስድስተኛ ደረጃን ላይ ይገኛል። የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍ ከኋላ የሚከተሉት ቡድኖች እንዳይደርሱበት ያደርገዋል እንጅ የደረጃ ለውጥ ግን አያስገኝለትም።
ሁለቱ ቡድኖች እ.አ.አ ከ2003 ወዲህ በተገናኙባቸው 33 የላሊጋ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ በ27 ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል።
ሴልታ ቪጎ ያሸነፈው በአራት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የሴልታ ቪጎ አሠልጣኝ ጊራልዴዝ ሪያል ማድሪድ በቅርብ ጊዜ ተደጋጋሚ ሽንፈት ቢደርስበትም አደገኛ ቡድን መኾኑን እናውቃለን ብለዋል።
ዛሬ ታላቁን ቡድን ለማሸነፍ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። ላሊጋውን ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ በቅደም ተከተል ይመሩታል።
ማዮርካ፣ ሌቫንቴ እና ሪያል ኦቪዲዮ ወራጅ ቀጣው ውስጥ ይገኛሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



