ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ቶትንሃም ከክሪስታል ፓላስ 62ሺህ 850 ተመልካች በሚይዘው በቶትንሃም ሆትስፐር ስታዲየም ምሽት 5:00 ይጫወታሉ።
ቶትንሃም ከ28 ጨዋታዎች 29 ነጥብ በመያዝ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን 32 በማድረስ አንድ ደረጃ ከፍ የሚል ይኾናል።
ተጋጣሚው ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ከ28 ጨዋታዎች 35 ነጥብ በመሠብሠብ ደረጃው 14ኛ ነው።
ጨዋታውን ድል ካደረገም 13ኛ ደረጃን ከብራይተን መረከብ ያስችለዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ በ29 ጨዋታዎች ተገናኝተው ቶትንሃም በ19 ጨዋታዎች ድል በመንሳት የበላይነቱን አሥመሥክሯል።
ክሪስታል ፓላስ ደግሞ በስድስት ጨዋታዎች አሸንፏል፤ ሁለቱ ቡድኖች በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ከላይ ከተጠቀሰው አሃዝ ውስጥ ቶትንሃም በሜዳው 16 ጨዋታዎችን አድርጎ የተሸነፈው በሦሥት ጨዋታዎች ብቻ ሲኾን በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።
የቶትንሃሙ አሠልጣኝ ኢጎር ቱዶር ጥሩ ልምምድ ሠርተናል። የተጫዋቾች ሥነ ልቦና ከፍ ብሏል። ቡድኑ ይወርድ ይኾን? የሚለውን ጫና ተቋቁመን እንጫወታለን ብለዋል።
አሠልጣኙ አክለውም በደጋፊዎቻችን ታግዘን ጨዋታውን ስለምናደርግ ከወራጅ ቀጣናው የምንርቀበትን ነጥብ እናስመዘግባለን የሚል አቋም አለኝ ነው ያሉት።
የክሪስታል ፓላሱ ማናጀር ኦሊቨር ግላስነር ” ዛሬ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስ የምናደርገው ጨዋታ ነው። ማሸነፍን ብቻ ዓላማ አድርገንም እንጫወታለን” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሊጉን አርሰናል በ67 ነጥብ እየመራው ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በ60 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በ51 ነጥብ ሦሥተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዌስት ሃም፣ በርንሌይ እና ዎልቭስ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ሲል ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!



