በሊጉ ለመቆየት ጭላንጭል ተስፋ ባለው እና ለዋንጫ በሚፎካከር ቡድን መካከል የሚደረግ ጨዋታ።

0
10
ባሕር ዳር፡ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርስ እና አስቶን ቪላ ምሽት 5:00 ይጫወታሉ።
ዎልቭስ ከ28 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በሰባቱ አቻ ተለያይቶ፣ በ20 ተሸንፎ 10 ነጥብ በመያዝም የሊጉን የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ይገኛል።
በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋ ብቻ ያለው ዎልቭስ ዛሬ ላለመውረድ እየተሟጠጠ የሚገኘውን ዕድሉን ነፍስ ለመዝራት ነው የሚጫወተው።
ተጋጣሚው አስቶን ቪላ 51 ነጥብ በመሠብሠብ ሦሥተኛ ደረጃ በመያዝ አንድም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ዝቅ ሲልም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ተሳታፊ ለመኾን ይጫወታል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍ የደረጃ ለውጥ ባያመጣም በሊጉ በሁለተኛነት ከተቀመጠው ማንቸስተር ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት ከአምስት ወደ ሁለት ለማጥበብ ያስችለዋል።
በሌላ በኩል ከኋላው በሚከተለው ማንቸስተር ዩናይትድ እና በአስቶን ቪላ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ሦሥት ብቻ ነው። በመኾኑም ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታውን እሑድ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የሚያደርግ ሲኾን ቪላ ዛሬ ካሸነፈ ከቀያይ ሰይጣኖች የሚኖረው የነጥብ ልዩነት እንዲሰፋ ያደርጋል።
ዎልቭስ በሜዳው ከአስቶን ቪላ ጋር ካደረጋቸው የቅርብ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ በማሸነፍ የበላይ ነው። በጠቅላላው ሁለቱ ቡድኖች በ21 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ተገናኝተው ዎልቭስ በሰባቱ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አስቶን ቪላ ደግሞ በስምንት ጨዋታዎች ድል አድርጓል። በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል ሲል ኤአይስኮር ዶት ኮም አስነብቧል።
ዛሬ ዎልቭስ ላለመውረድ ያለውን ጭላንጭል ተስፋ ለማለምለም፣ አስቶን ቪላ ደግሞ አንድም የዋንጫ ተፎካካሪ ኾኖ ለመዝለቅ በሌላ በበኩል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የሚያደርገውን ነጥብ ከወዲሁ ለመሠብሠብ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ተጠብቋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here