“የባየር ሙኒክ ብቻ በሚመስለው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ አዲስ ነገር ከባየር ሊቨርኩሰን”

0
425

ባሕርዳር: የካቲት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጀርመን እግር ኳስ የባየር ሙኒክን ያህል የደመቀ እና የሚያስቀና ታሪክ ያለው ቡድን አይገኝም። የቡንደስ ሊጋ ዋንጫን ለ 33ኛ ጊዜ በመሳም ውጤታማው ክለብ ነው።

ባለፉት 11 ዓመታት በተከታታይ ዋንጫውን ማንሳቱም የጥንካሬው ግልጽ ማሳያ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ከባየርሙኒክ ቀጥሎ የሚጠራው ቡድን ቦርሲያ ዶርትሙንድ ነው። ነገር ግን የሊጉን የአንድ ቡድን ሩጫ ማስቆም አልቻለም።

እንዲህ የሙኒክ ብቻ በመሰለው የጀርመን እግር ኳስ ዘንድሮ አዲስ ነገር እየታየበት ነው። ኀያሉ ባየር ሙኒክም ግርማው ቀሎ እየታየ ነው።
የዦቪ አሎንሶው ባየር ሊቨርኩሰን አሁን ከሙኒክ በላይ ተቀምጧል። በሊጉ ጅማሮ የታየው የሊቨርኩሰን እና አሎንሶ ጥንካሬ ስለመዝለቁ የተጠራጠሩ ሁሉ ላይ ጨርስ አለመጀመሩን እያመኑ ነው።

ሊቨርኩሰን በ 22 የቡንድስ ሊጋ ጨዋታ 58 ነጥብ ላይ ደርሷል። በአራት ጨዋታ ነጥብ ከመጋራቱ ውጭ ሽንፈት አላስተናገደም። ባየር ሙኒክ በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር ያሸነፈው 16 ሲኾን፣ በአራቱ ሽንፈትን አስተናግዶ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

አሁን ባየር ሊቨርኩሰን ከሙኒክ በስምንት ነጥብ በልጦ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የአሎንሶው ቡድን ሁሉንም ሲረታ፣ የቶማስ ቱሸሉ ሙኒክ በሁለቱም ፈተናውን ወድቋል።

ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ ሙኒክ ጨዋታውን አሸንፎ የነጥብ ልዩነቱን እንደሚያጠብ ቢጠበቅም ነገሩ በተቃራኒው ኾኖ የሊቨርኩሰን የበላይነት ሰፍቷል።
ከዚህ ጨዋታ ሳምንት በኋላም የዣቪው ቡድን ድሉን ሲደግም በሚዛኑ የማይገኘው ሙኒክም ሽንፈቱን ደግሞታል።

የሙኒክ መድክም ሳያንስ የባየር ሊቨርኩሰን የተለየ ጥንካሬ ምን አልባት በጀርመን እግር ኳስ ከዓመታት በኋላ አዲስ ነገር የሚታይ ይመስላል። በተጫዋችነት እንጅ በአሠልጣኝነት ያልተወራለት አሎንሶ እና ቡድኑም የሙኒክን የበላይነት ለመግታት እየገሰገሱ ነው።

ይሄ እውን ኾኖ ሊቨርኩሰን ዋንጫውን ካነሳም የእንግሊዛዊ አጥቂ ሀሪ ኬን ጉዳይ መነጋገሪያ መኾኑ አይቀርም። ኬን በግል ለዓመታት ድንቅ እና ወጥ ብቃት በማሳየት ጥሩ የእግር ኳስ ታሪክ ያለው ቢኾንም ዋንጫ ግን አንስቶ አያውቅም።

ባለፈው ዓመት ቶትንሃምን ለቆ ባየርሙኒክን ሲቀላቀልም ዋንጫ ለማግኘት በማሰብ ነው። ተጫዋቹ “ደካማ”ወደሚባለው ቡንደስ ሊጋ የተዘዋወረው በቀላሉ ዋንጫ ለማንሳት ነው በሚልም ትችቶች ደርሰውበታል። ነገር ግን በቀላሉ ያሳካዋል በተባለው የቡንደስ ሊጋ ዋንጫ ላይ አሁን ባየር ሊቨርኩሰን እንቅፋት ኾኖ ፊቱ ላይ ቁሟል።

ዘጋቢ፦አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here