ግምቶችን ከንቱ ያደረገው የትንሿ ከተማ ክለብ።

0
26

 

አዲስ አበባ: የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከአርክቲክ ክበብ በ70 ማይል ርቀት ላይ የሚገኘው የኖርዌዩ ቡድን ቦዶ/ግሊምት፣ ትልልቅ ቡድኖችን በማሸነፍ ስሙ የታወቀ ቢኾንም ምሽት በሚላን ስታዲየም ያሳየው ውጤት ግን በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ውስጥ ካዩት ትልልቅ አስገራሚ ክስተቶች አንዱ ኾኖ ተመዝግቧል።

ከዘጠኝ ወራት በፊት በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በፒኤስጂ የተሸነፈውን እና የሦስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የኾነውን ኢንተር ሚላንን መግጠም ለቦዶ ከባድ ፈተና ነበር። ምንም እንኳን በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 3ለ1 በኾነ ውጤት መምራት ቢችሉም ጨዋታው አስፈሪ ነበር።

ኾኖም ቦዶ/ግሊምት በምድብ ድልድል ማንቸስተር ሲቲን እና አትሌቲኮ ማድሪድን እንዳሸነፈው ሁሉ አሁንም ለታላቅ ዓላማ ተነሳ። በጣሊያን ምድር ያሳዩት ብቃት የክርስቲያን ቺቩን ቡድን (ኢንተር ሚላን) በደርሶ መልስ ለማሸነፍ ያስቻለ ቆራጥ እና የማይበገር ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የኢንተርን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲከላከሉ የቆዩ ሲኾን በመቀጠልም ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የሴሪ ኤ መሪዎቹን ተስፋ አስቆርጠዋል።

በምሽቱ ጨዋታ 2ለ1 በማሸነፍ በድምር ውጤት 5ለ2 በኾነ ውጤት ቦዶ/ግሊምት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ 16ቱ ውስጥ መግባት ችሏል።

ቀጣይ ከማንቸስተር ሲቲ ወይም ከስፖርቲንግ ጋር ይጫወታሉ። የቡድኑ አሠልጣኝ ኬቲል ኑትሰን “ይህ ለቦዶም ኾነ ለኖርዌይ እግር ኳስ ታሪካዊ ቅጽበት ነው” ብለዋል። የቡድኑ ኮከብ ጄንስ ፔተር ሀውጌ አሁንም አነሳሽነቱን አሳይቷል። በውድድሩ የዘንድሮ ስድስተኛ ጎሉን በማስቆጠር መሪ ያደረጋቸው ሲኾን ለሀኮን ኢቭጄን ሁለተኛ ጎልም አመቻችቶ አቀብሏል።

ቀደም ሲል በኤሲ ሚላን ለሁለት ዓመታት ተጫውቶ በነበረበት ወቅት ሳን ሲሮ ስታዲየም የተመለሰው ሀውጌ “እውነት አይመስልም፤ ግን አሁን ከታላላቅ ቡድኖች ጋር እዚያው ደርሰናል። ቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ምን ይዘው እንደሚመጡ ማየት በጣም አስደሳች ይኾናል ሲል ደስታውን ገልጿል።

ቦዶ በመጀመሪያዎቹ ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ድል ባለመቀናቱ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በማንቸስተር ሲቲ እና በአትሌቲኮ ማድሪድ ላይ ድል የግድ ያስፈልገው ነበር። በመሆኑም ይህ “የተረት ያህል” ድንቅ የኾነ ጉዞ ለቡድኑ የማይታሰብ መስሎ ታይቶ ነበር።

ኾኖም ግምቶችን ሁሉ በመቀልበስ ውጤቱን አሳካ። በፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ላይ የተቀዳጁት የ3ለ1 ድል ተገቢውን ትኩረት እና አድናቆት አስገኝቶላቸዋል። ነገር ግን ይህ ድል በአጋጣሚ የመጣ አልነበረም። ቦዶ አትሌቲኮ ማድሪድን በሜዳው 2ለ1 በማሸነፍ የማጣሪያውን ቦታ ማረጋገጥ ችሏል።

የአሠልጣኝ ኑትሰን ቡድን ባለፈው የውድድር ዘመን በዩሮፓ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በቶትንሃም ተሸንፎ ነበር። ለስኬታቸው ቁልፉ የገዛ ሜዳቸውን ለተቃራኒ ቡድኖች እጅግ ፈታኝ የማድረግ ችሎታቸው እንደኾነም ይነገራል።

በሰሜን ኖርዌይ የሚገኘው የቦዶ አካባቢ በረጅሙ የክረምት ወራት ቅዝቃዜው የበረታ በረዷማ እና ነፋሻማ ሲኾን የሙቀት መጠኑም ከዜሮ በታች እጅግ ዝቅ ይላል። ይህ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ቡድኑ በሰው ሠራሽ ሜዳ ላይ እንዲጫወት ያስገደደው ሲኾን በተፈጥሮ ሳር ላይ መጫወት ለለመዱ ቡድኖች ደግሞ ይህ ትልቅ ፈተና ነው።

እነዚህ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ከተጫዋቾቹ ቆራጥነት እና በራሳቸው ላይ ካላቸው ጠንካራ እምነት ጋር ተዳምረው ብዙ ታላላቅ ቡድኖች ከቦዶ ሜዳ በሽንፈት እንዲመለሱ አድርገዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት በጆሴ ሞሪንሆ የሚመራውን ሮማን 6ለ1 በኾነ ውጤት ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲኾን ሴልቲክ፣ ቤሺክታሽ፣ ፖርቶ እና ላዚዮም በቅርብ ዓመታት የዚሁ ሰለባ ኾነዋል።

የቡድኑ አምበል ፓትሪክ በርግ ለካናል ፕላስ ሲናገር “ይህ አስደናቂ ነው! ለክለቡም ኾነ ለከተማዋ ማመን የሚያስቸግር ስኬት ነው። ሰዎች ማንቸስተር ሲቲን፣ አትሌቲኮን እና አሁን ደግሞ ኢንተርን ሁለት ጊዜ እናሸንፋለን ብለው የገመቱ አይመስለኝም። እጅግ ድንቅ ውጤት ነው” ብሏል።

ይህ ለቦዶ/ግሊምት ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ውስጥ የሚሳተፉበት አዲስ እና ያልታወቀ ምዕራፍ ነው። ይህ ጉዟቸው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል ባይታወቅም በሳን ሲሮ ስታዲየም ቢጫ በለበሱ እና ስካርፋቸውን ከፍ አድርገው በያዙ ደጋፊዎቻቸው በታጀበው ጩኸት መደገፋቸውን ይቀጥላሉ።

አሠልጣኝ ኑትሰን “በጣም ኮርቻለሁ እኛ የመጣነው ከአንዲት ትንሽ ከተማ ነው” ብለዋል። እኛ ማድረግ ከቻልን ሁሉም ሰው ማድረግ እንደሚችል ማሳየት እንደቻል ተስፋ አደርጋለሁ። ለእኔ የዚህ ሁሉ ታሪክ እጅግ ውብ የኾነው ነገር ይሄ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ቦዶ ወደ ሩብ ፍጻሜው ለመግባት ከማንቸስተር ሲቲ ወይም ከስፖርቲንግ ጋር ይጫወታሉ።

በቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here