ባሕር ዳር: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ምሽት1:30 ላይ አርሰናል ከቶትንሃም ይጫወታል።
አርሰናል ከ22 ዓመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ለማሳካት ቶትንሃም ደግሞ ላለመውረድ ብርቱ እና ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ኒውካስትል ዩናይትድን 2ለ1 ማሸነፉን ተከትሎ በአርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ጠቧል።
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም ማንቸስተር ሲቲ በመጨረሻዎቹ 12 ጨዋታዎች ከአርሰናል የተሻለ ነጥብ የመሰብሰብ ልማድ አለው።
አርሰናል “የፊተኞቹ ኋላ፤ የኋለኞቹ ፊት” ዓይነት ብሂል የሊጉ መሪ ቢኾንም በቅርብ ሳምንታት ያሳየው ብቃት ደጋፊዎቹን አላስደሰተም። መሪነቱን አስጠብቆ ጨዋታን የመጨረስ አቅሙ ለመዳከሙ ከወልቭስ ጋር ያደረገው ጨዋታ አንዱ ማሳያ ነው።
አሠልጣኝ አርቴታ “አሁን ያለንበት ሁኔታ ጥሩ ነው” ቢሉም ዛሬ ከቶትንሃም የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሏቸዋል እየተባለ ይገኛል።
አሠልጣኙ ከወልቭስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያጡትን ነጥብ ለማካካስ በሰሜን ለንደን ደርቢ ዛሬ ቶትንሃምን ማሸነፍ አለብን ነው ያሉት።
ተጫዋቾች በወልቭስ ከደረሰባቸው የመንፈስ ስብራት ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስ ዝግጁ ናቸው ማለታቸውን ስካይ ስፖርት አስነብቧል።
ለአርሰናል ካይ ሃቨርዝ እና ማርቲን ኦዴጋርድም ከጉዳታቸው ተመልሰዋል፡፡
ቶትንሃም በሊጉ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ፣ በስምንቱ አቻ ተለያይቶ እና በ11 ጨዋታዎች ተሸንፎ 29 ነጥብ በመያዝ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በዚህ ይዞታው ከቀጠለ የመወረድ አደጋ ያንዣበበበት ቶትንሃም ቶማስ ፍራንክን አሰናብቶ የ47 ዓመቱን ኢጎር ቱዶር መሾሙ ይታዎቃል።
አዲሱ አሠልጣኝም “ቶትንሃምን መቶ በመቶ በፕሪምየር ሊጉ እንዲቆይ አደርጋለሁ፤ የሥራየ የመጀመሪያ ዕቅድም አርሰናልን ማሸነፍ ነው ። ለዚህም ክፍተቶችን ለይተን ሥልጠና አድርገናል ብለዋል።
በቶትንሃም በኩል ክርስቲያን ሮሜሮ በቅጣት አይሰለፍም።
ዛሬ በሚደረገው 199ኛ ሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል አሸንፎ የዋንጫ ግስጋሴውን ያጠናክራል? ወይስ በአዲስ አሠልጣኝ ለደርቢውን የሚጫወተው ቶትንሃም አሸንፎ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ያለመልም ይኾን? ምሽት1:30 የሚደረገው ጨዋታ ምላሹን ይሰጠናል።
በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ቀን 11:00 ላይ ክሪስታል ፓላስ ከወልቭስ፣ ኖቲንግሐም ፎረስት ከሊቨርፑል፣ ሰንደርላንድ ከፉልሃም ይጫወታሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



