ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታን ያደርጋል።

0
25

 

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በተለይ 52 ሺህ 900 ተመልካች በሚታደምበት ኢትሃድ ስታዲየም ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት 5:00 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂም፣ አጓጊም ኾኗል።

ማንቸስተር ሲቲ ከ26 ጨዋታዎች 53 ነጥብ በመያዝ ከመሪው አርሰናል በአምስት ነጥብ ርቆ ነው የሚጫወተው። ይህን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ለማጥበብ ከኒውካስትል ዩናይትድ የሞት ሽረት ግጥሚያ የሚያደርግ ይኾናል ሲል ያስነበበው ዘ ኢንዲፔንዳንት ነው።

ያም አለ ይህ የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ጋርዲዮላ ፕሪሚየር ሊጉ 12 ጨዋታዎች እየቀሩት አሁን ላይ ስለ ዋንጫው አላስብም ነው ያሉት።

የማስበው እና ዕቅድ የምነድፈው የዛሬውን የኒውካስትል ዩናይትድ ጨዋታ እንዴት እንደምናሸንፍ ብቻ ነው ብለዋል።

ይህን የአሠልጣኙን ሐሳብ ዴይሊ ሜይል ጋርዲዮላ ጨዋታው ላይ ትኩረት አደርጋለሁ ማለታቸውን በተለያዬ መንገድ መተርጎሙን አስነብቧል።

የመጀመሪያው የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እናጠባለን ነው ያሉት። በቀጣይ የሚኖሩ ጨዋታዎችንም በማሸነፍ ዋንጫውን የምንወስደው እኛ ነን ማለታቸው ነው የጠቆሙት።

በረዥም ርቀት የሩጫ ውድድር ፈጥኖ ጀምሮ የሮጠ አትሌት መች ያሸንፍና! ማንቸስተር ሲቲን በነጥብ በልጦ የሚገኘው ቡድን እጣ ፈንታም ከዚህ ያለፈ አይደለም በማለት አርሰናልን ለመወረፍ ነው ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት በትንታኔው አስነብቧል።

ዜጎቹ በሜዳቸው ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ካደረጓቸው 21 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች 16ቱን አሸንፏል። በሁለቱ ብቻ ሲሸነፍ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል።

ከሜዳው ውጭ ደግሞ በ28 ጨዋታዎች ተገናኝተው በ15 ጨዋታዎች አሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች ነው በኒውካስትል የተሸነፈው። በጠቅላላው በፕሪሚየር ሊጉ ሁለቱ ቡድኖች 47 ጨዎታዎችን አድርገው ማንቸስተር ሲቲ በ31 አሸንፎ የበላይ ነው ።

ኒውካስትል ማሸነፍ የቻለው በስምንት ጨዋታዎች ብቻ ሲኾን በስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ለማንቸስተር ሲቲ ማቲዮ ኮቫችች፣ ጆስኮ ግቫርዲዮል፣ ጄርሚ ዶኩ እና ሳቪኒኾ አይሰለፉም።

ኒውካስትል ዩናይትድ ከ26 ጨዋታዎች በ36 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈም ደረጃውን የሚያሻሽል ይኾናል።

ቡድኑ ከሰሞኑ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ካራባግን 6 ለ 1 በማሸነፉ ጥንካሬውን ያመላክታል።

ይህን የአሸናፊነት መንፈስ ሰንቆ የሚጫወተው ኒውካስትል ዩናይትድ ዛሬ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ተጠብቋል።

ጋርዲዮላ “ስለዋንጫው ሳይኾን ስለዛሬው ጨዋታ ብቻ ነው የማስበው” ማለታቸው ጨዋታው እንዳሰጋቸው አመላካች አስተያየት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ኢሚል ክራፍዝ፣ ቡሩኖ ጉማሬሽ፣ ፋቢያን ሼር እና ቲኖ ሊቨርሜንቶ ለኒውካስትል ዩናይትድ የማይሰለፉ ተጨዋቾች ናቸው።

በጨዋታው ማንቸስተር ሲቲ አሸንፎ ለአርሰናል ስጋት ይኾን ወይስ ኒውካስትል ዩናይትድ ድል አድርጎ አንድም ደረጃውን ያሻሽል ይኾን፤ ሁለትም የአርሰናልን የዋንጫ ማንሳት ተስፋ ያጎመራለት ይኾን?

በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በጉጉት የሚጠብቀው እና ምሽት 5:00 ላይ የሚጀመረው ጨዋታ ምላሹን ይነግረናል።

በሌሎች ጨዋታዎች፦
ምሽት 12:00 ላይ

👉 አስቶን ቪላ ከሊድስ
👉 ቼልሲ ከበርንሌይ
👉 ብሬንትፎርድ ከብራይተን ይጫወታሉ።

ምሽት2:30 ላይ ደግሞ
👉 ዌስት ሃም ከቦርንማውዝ የሚጫወቱ ይኾናሉ።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here