የጣናው ሞገድ ወደላቀ አሸናፊነት ይመለስ ዘንድ ምን እየተሠራ ነው?

0
19

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ቡድን በ1973 ዓ.ም ነበር የተመሠረተው።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር። በጥንካሬውም ልቆ በመውጣት ፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅሎ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።

“የጣናው ሞገድ” ቅጽል ስሙ ነው፤ በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ ውጤት በማስመዝገቡ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ እንደነበር አይዘነጋም።

👉ዛሬስ?

የቡድኑ ደጋፊ መኾኑን የነገረን ወጣት ቢኒያም ተሾመ ቡድኑ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ሁሉ በሚያገኛቸው የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች እና በአካል ይከታተላል።

እርሱ እንደሚለው የጣናው ሞገድ ከዓመት ዓመት እየተዳከመ መጥቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት በቡድኑ የጨዋታ ዋዜማ እና ማግሥት ስለጨዋታው የማይነጋገር ደጋፊ አልነበረም የሚለው ወጣት ቢኒያም አሁን ግን ውጤት በመጥፋቱ እና የአጨዋወት ለዛው በመሟጠጡ ደጋፊው ተስፋ ቆርጦ ወደ መርሳቱ ተቃርቧል ይላል።

እኛም መጣት ቢኒያምን “ለውጤት መጥፋት ምክንያቱ ምንድን ነው ብለህ ትገምታለህ? ” ብለን ጠይቀነዋል።

በተለይ በ2018 የውድድር ዘመን ቡድኑ በተጫዋቾች ዝውውር ንቁ ተሳታፊ ኾኖ ወሳኝ ተጫዋቾችን አለማስፈረሙ ጎድቶታል ባይ ነው።

አዳዲስ ተጫዋቾችን ማምጣት ባይችል እንኳ ስመ ጥር ተጫዋቾችን ማቆየት አለመቻሉ ለውጤት መጥፋት አስተዋጽዖው ከፍተኛ ነው ብሏል።

በቡድኑ በተለይ ከፊት ኾኖ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች አለመኖሩ ዋጋ አስከፍሎታልም ነው ያለው።

በየጊዜው የሚደረጉ ጨዋታዎችን ገምግሞ ስህተቱን በመለየት ፈጣን መፍትሔ እየተበጀም አይደለም ባይ ነው ወጣት ቢኒያም።

በቀሪው የውድድር ጊዜ ቡድኑ ውጤታማ ይኾን ዘንድም ቢረፍድም እንኳ ሳይመሽ የአጥቂ ባህርይ ያላቸውን ተጫዋች ማስፈረም ይኖርበታል ሲል አስተያዬቱን ሰጥቷል።

የባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ቡድን ሥራ አሥኪያጅ ልዑል ፍቃዱ እንዳሉት ቡድኑ ከ19 ጨዋታዎች በ12 አቻ ሲለያይ ማሸነፍ የቻለው በአራት ጨዋታዎች ብቻ ነው። ከ20 ቡድኖች ዘጠነኛ ደረጃ ላይም ይገኛል ብለዋል።

ቡድኑ መለያውን ለብሶ ዘምሮ የማይሰለች፣ ተጉዞ የማይደክም የአያሌ ደጋፊዎች ባለቤት ነው ያሉት አቶ ልዑል የጣናው ሞገድ በአግባቡ ይከላከላል። የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾችም ብቃት ያላቸው ናቸው ብለዋል።

ሥራ አሥኪያጁ አክለውም የመስመር ኳስን ከቀኝ እና ግራ ወደ ሳጥን የሚያሻግሩ ምርጥ ተጫዋቾችም አሉን ነው ያሉት።

“ነባሮቹ ምርጥ አጥቂዎች እኛ ጋር መቆየት ቢፈልጉም የጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ ስለነበር ማቆየት አልቻልንም” ብለዋል። በእነርሱ ምትክ በአጥቂ ሥፍራ የተመደቡ ተጫዋቾች ግን የልምድ ማነስ፣ የአካል ብቃት ውስንነት፣ የደጋፊዎችን እና የሌሎችንም ጫና መቋቋም ያለመቻል ችግሮች እንደነበሩባቸው በግምገማ መለየቱን ተናግረዋል።

በመፍትሔነትም አሁን ላይ ሁነኛ አጥቂዎችን ወደ ቡድኑ መቀላቀላቸውን አቶ ልዑል ተናግረዋል።

አዳዲስ ተጫዋቾችን ከመጨመር ባለፈ ቡድኑን በቴክኒክ፣ በታክቲክ ሥልጠና እንዲሁም በሥነ ልቦና የማብቃት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

ከ20ኛው ሳምንት ጀምሮ በሚኖረው ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማ በውብ ጨዋታ ውጤታማ ይኾናል የሚል ጽኑ ተስፋ መሰነቃቸውንም ተናግረዋል።

የቡድኑ የበላይ ጠባቂ የኾኑት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እናጎሹ እንዳላማው ቡድኑ በዚህ ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ አጥጋቢ ውጤት አለማምጣቱን ተናግረዋል። ምክንያቱ ደግሞ የአጥቂ ክፍተት መኖሩን በግምገማ ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድን የሀገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ያወጣውን የፋይናንስ ሥርዓት ያከብራል ያሉት አቶ ጎሹ የፋይናንስ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተጫዋቾች በዝውውር እንዲመጡ ቦርዱ ውሳኔ ማሳረፉን ጠቁመዋል።

በመኾኑም በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ውጤታማ ይኾናል የሚል ተስፋም አላቸው።

ዘጋቢ፦ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here