የፈረስ ስፖርት እንዲያድግ ምን ተሠራ?

0
55
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፈረስ ስፖርት የየሀገራትን ባሕል ጨምሮ ዝላይ፣ እሽቅድድም፣ አለባበስ፣ ፖሎ፣ አክሮባት እና የሰረገላ ውድድር የሚሰኙት ያካትታል፡፡
የፈረስ ውድድር በአግባቡ ከተሠራበት እንደ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ እና መሰል ስፖርቶች ሁሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መኾኑን ጥናቶች እና ነባራዊ እውነታዎች ያመላክታሉ፡፡
ከፈረስ ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላት ኢትዮጵያ ግን ከጭነት እና ከበዓላት ማድመቂያነት ያለፈ ለተሻለ ገቢ ማግኛነት አልተጠቀመችበትም፡፡
አለቃ አብዬ ሙሉነህ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፈረሰኛ እና የፈረስ ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡
በበዓላት የፈረስ ሰላምታን (ትርኢትን) ማሳየት ከጀመሩ ስምንት ዓመት ኾኗቸዋል፡፡
በውጪ ሀገራት የሚካሄደውን የፈረስ ስፖርት በቴሌቪዥን እንደሚከታተሉ እና እንደሚስባቸውም ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርትና ተመራማሪ ብርሃኔ አሥራት (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከፈረስ ጠንካራ ቁርኝት እና ለስፖርቱም ምቹነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
የፈረስ ስፖርት ከባሕላዊ ስፖርቶች ውስጥ እንደሚመደብ ገልጸው ባለው ምቹ ኹኔታ ልክ ግን እንዳልተሠራበትም ጠቅሰዋል፡፡
በዓለም አቀፉ መድረክ የፈረስ ስፖርት ፌዴሬሽን ዘጠኝ ዓይነት ውድድሮች እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡
ጀርመን፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ በስፖርቱ ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው፡፡ በአፍሪካም ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ እና አልጀሪያ ይጠቀሳሉ፡፡
የፈረስ ስፖርት በትኩረት ከተሠራበት ለሥራ እድል ፈጠራ እና ለቱሪስት መስህብነት እንደሚያገለግል ነው ዶክተር ብርሃኔ የገለጹት፡፡
በዘርፉ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ስፖርቱ ያለውን እምቅ ሃብት ያመላከቱ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያም እንደ ሌሎች ሀገራት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትኾን ስፖርቱን ራሱን አስችሎ ማዋቀር፣ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ፣ ባሕላዊ ሕጎችን ከዘመናዊው ማስተሳሰር፣ ክለቦችን በመፍጠር ማደራጀት እና ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠይቅ ነው ያመላከቱት፡፡
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጋሻው ተቀባ በአማራ ክልል ለፈረስ ስፖርት ምቹ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ካለው የፈረስ ሃብት እና ምቹ ከባቢ አንጻር ሲታይ በአቅሙ ልክ አልተሠራበትም ብለዋል።
የፈረስ ስፖርትን በማሳደግ ለመጠቀምም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን መቃኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከባሕል ውድድሮች በተጨማሪ በየክልሎቹ የፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ማቋቋም እና ማወዳደር፣ ጥናት ማድረግ፣ ተፈላጊ የፈረስ ዝርያዎቹን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት እና ልምድ በመቅሰም መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ የባሕል ስፖርቶች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሕይወት መሐመድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ባሕላዊ የፈረስ ውድድር ሕግ ወጥቶለት እንደሚከናወን አንስተዋል፡፡
ጉግስ እና ሽርጥም እየተካሄዱ ያሉ ውድድሮች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የትኛውም ስፖርት መነሻው የሀገራት ባሕል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ የኢትጵያ ፈረስ ስፖርትንም ለማሳደግ ባሕላዊውን ማዳበር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
ፌዴሬሽናቸው ባሕላዊ ስፖርቶችን ለማዳበር በየክልሉ ፌዴሬሽኖች ተቋቁመው ውድድሮች እየተደረጉ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ስፖርቱን ለማሳደግ በእቅድ እየሠራን ነው፤ ዘንድሮ የአፍሪካ የባሕል ስፖርት ፌስቲቫልን በማስተናገድም ልምድ እናሳድጋለን፤ የፈረስ ስፖርትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል፡፡
የባሕላዊ ስፖርቱን አደረጃጀት እያጠናከርን ነው፤ እስከ 2030 ባሕላዊ ስፖርቶችን ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡
በየትኛው ሀገር ስፖርት የሚያድገው በባለድርሻ አካላት እና በሕዝብ ተሳትፎ ነው፤ መንግሥትም ለስፖርቱ ትኩረት በመስጠት ፖሊሲ በማውጣት እና በማስተዋወቅ ኅብረተሰቡን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡
ፌዴሬሽናቸው መንግሥት እና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከባለድርሻዎች ጋር በመተባበር የባሕል ስፖርቶችን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here