ባሕር ዳር: የካቲት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በሊጉ 26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ማንቸስተር ሲቲ ከፉልሃም፣ አስቶን ቪላ ከብራይተን እንዲኹም ሰንደርላንድ ከሊቨርፑል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አጓጊ እና ተጠባቂ ኾነዋል። ጨዋታዎቹ ምሽት 4:30 ላይ ይደረጋሉ።
በተለይ ማንቸስተር ሲቲ ከፉልሃም በኢትሃድ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ለማንቸስተር ሲቲ እጅግ ወሳኝ ነው።
ዜጎቹ ከ25 ጨዋታዎች 50 ነጥብ በመሠብሠብ እና ከሊጉ መሪ አርሰናል በስድስት ነጥብ ርቆ በሁለተኛነት እንደመገኘታቸው ነጥቡን ለማጥበብ እና የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ለማጠናከር ወሳኝ ነው።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃውን አስጠብቆ ለመቀጠል ይረዳዋል።
ተጋጣሚው ፉልሃም ከ25 ጨዋታዎች በ10 አሸንፎ፣ በአራት አቻ ተለያይቶ፣ በ11 ተሸንፎ እና 34 ነጥብ በመያዝ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ጨዋታውን ካሸነፈ ሁለት ደረጃዎችን የሚያሻሽል ይኾናል።
ሁለቱ ቡድኖች በቅርብ ከተገናኙባቸው 35 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ማንቸስተር ሲቲ በ22ቱ በማሸነፍ የበላይ ነው።
ፉልሃም ማንቸስተር ሲቲን ድል የነሳው በአራት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ለሁለቱም ቡድኖች በጣም ጠቃሚ ነው።
በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ አስቶን ቪላ ከብራይተን ምሽት 4:30 ላይ ይጫወታሉ።
አስቶን ቪላ ከ25 ጨዋታዎች 47 ነጥብ በመያዝ እና ከማንቸስተር ሲቲ በሶስት ነጥብ ርቆ በሶስተኛነት ተቀምጧል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃውን አስጠብቆ ይቀጥላል ማለት ነው። ተጋጣሚው ብራይተን በ31 ነጥብ 14ኛ ነው። ጨዋታውን ድል ካደረገ ደረጃውን ከፍ የሚያደርግ ይኾናል።
ምሽት 5:15 ላይ ደግሞ ሰንደርላንድ ከሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ አጓጊ ነው።
ቀያዮቹ ከ25 ጨዋታዎች 39 ነጥብ በመያዝ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ ደረጃውን በማስጠበቅ ቀጣይ ጉዞው የሚረዳው ይኾናል።
ባለሜደው ሰንደርላንድ ደግሞ በ36 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ካሸነፈ አራት ደረጃን ያሻሽላል። ሰንደርላንድ ጥሩ ስብስብ የያዘ በመኾኑ ዛሬ ሊቨርፑልን ይፈትነዋል የሚሉ በርካታ ናቸው።
የሊቨርፑል አሠልጣኝ ኧርኔ ስሎት ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት የዘንድሮ የውድድር ዓመት አስቸጋሪ እንደኾነባቸው አልሸሸጉም። ይህም ኾኖ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እጥራለሁ ነው ያሉት።
በሌሎች የምሽት 4:30 ጨዋታዎች፦
ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስትሃም፣ ቼልሲ ከሊድስ ነጥብ መጋራታቸው ይታወሳል። ኒውካስትል ቶትንሃምን፣ በርንማውዝ ደግሞ ኤቨርተንን በተመሳሳይ 2ለ1 አሸንፈዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



