“ጠንካራው የባሕር ዳር ከተማ ቡድን ወደ ቀደመ ጥንካሬው ይመለሳል” የክለቡ ሥራ አሥኪያጅ ለዑል ፈቃደ።

0
504

ባሕር ዳር: የካቲት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ድምቀት ከኾኑ ክለቦች መካከል ባሕር ዳር ከተማ አንዱ ነው። ክለቡ የድንቅ ደጋፊዎች ባለቤት ሲኾን፤ በ2015 የውድድር ዘመን እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ለዋንጫው ተፋልሟል።

በሊጉ ሁለተኛ ኾኖ በማጠናቀቅ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመሳተፍ እድልም አግኝቷል። በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት በዚህ አሕጉራዊ መድረክ ለነገ ስንቅ የሚኾን እንቅስቃሴ በማድረግም በደጋፊዎቹ ተመሥግኗል።

የ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት ሲጀመር ለዋንጫ ከተገመቱ ቡድኖች መካከል የጣና ሞገዶቹ ቅድሚያ ካገኙት ውስጥ ናቸው። የክለቡ የመጀመሪያ ሳምንት ውጤቶችም በመልካም የሚነሱ ነበሩ።

ነገር ግን በቅርብ ጨዋታዎች ክለቡ ውጤት ርቆታል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በሁለቱ ነጥብ ሲጋራ በአራቱ በተከታታይ ተሸንፎ በክለቡ አካሄድ ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ ኾኗል።
የክለቡ ሥራ አሥኪያጅ ልዑል ፈቃደ በክለቡ ወቅታዊ የውጤት ቀውስ ዙሪያ ለአሚኮ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ባሕር ዳር ከተማ ከነበረበት ከፍ እንጅ ዝቅ ማለት አይመጥነውም፤ ወደ ውጤት ለመመለስም ችግሮችን ተነጋግረን ለይተናል ብለዋል። በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ውድድር ምክንያት በቂ ቅድመ ዝግጅት አለመደረጉ እና የተጫዋቾች ባልተገባ ሥነ ምግባር የካርድ ሰለባ ኾኖ ክለቡን አለማገልገል፤ የአጥቂ በተለይም የመስመር አጥቂ ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ መሳሳት ክለቡን ውጤት ያሳጡ ምክንያቶች ተብለው መገምገማቸውን አቶ ልዑል ገልጸዋል።

የክለቡ የመስመር ተጫዋች ዱሪሳ ከክለቡ መውጣቱ እና የአባስ መጎዳት ቡድኑ በመስመር ማጥቃት እንዲዳከም ማድረጉን በጉልህ አንስተዋል።
እነዚህ ችግሮች ቢለዩም ቡድኑ ይህን ያህል ሽንፈት ማስተናገድ አልነበረበትም በሚለው ሃሳብ ሁሉም የክለቡ አባላት መግባባት ላይ ደረሰውም መፋትሔዎች ተቀምጠዋል።
የክለቡን ውጤት ማጣት ተከትሎ በተለያየ መንገድ የሚነሱ አሉታዊ ሃሳቦች ትክክል አለመኾናቸውን ጠቁመዋል። አንዳንድ በግለሰብ ደረጃ የሚታዩ ችግሮች የግለሰቦች እንጅ አጠቃላይ የቡድኑ መንፈስ አይገልጹም ነው ያሉት።

ከዚህ በፊት የመስመር ተጫዋቹ ዱሪሳ ክለቡን የለቀቀበት መንገድ እና ሌላኛው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፍጹም ጥላሁን በቅርቡ ሜዳ ውስጥ ያሳየው ያልተገባ ባህሪ የመልበሻ ክፍሉ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

አቶ ልዑል ዱሪሳ በግሉ ምክንያት ከሀገር መውጣቱን እና ከሀገር ከመውጣቱ በፊት በአቋም መውረድ ተቀያሪ ከመኾኑ ውጭ የተፈጠረ ነገር የለም ብለዋል። በቅርቡ ሜዳ ላይ ሳይጎዳ ተጎዳሁ ብሎ ከሜዳ የወጣው ፍጹም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽሟል፤ ለጊዜው ከክለቡ ታግዷል፤ በቀጣይም ክለቡ አስተማሪ ቅጣት ያስተላልፋል ብለዋል።

በውድድሩ ሁለተኛ አጋማሽ “ጠንካራው የሕር ዳር ከተማ ቡድን ወደ ቀደመ ጥንካሬው ይመለሳል” ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ለዚህም ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞቹ እና የቡድኑ አመራሮች በግል እና በጋራ በመነጋገር ለውጤቱ አንቅፋት የነበሩ ጉዳዮችን ለማረም ቃል ተገብቷል ብለዋል።

የተጫዋቾችን ድካም ለመቀነስ እና በየቦታው ጤናማ ፉክክር እንዲኖር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት እንቅስቃሴ ስለመኖሩም ጠቁመዋል። በተለይ የመስመር አጥቂ እና ከአጥቂ ጀርባ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ጠቅሰዋል።

በቀሪ የፕሪሜየር ሊጉ ጨዋታዎች ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ተፎካካሪነት እንመለሳለን ከመሪዎቹ ያለው የነጥብ ልዩነትም ብዙ ሰፊ አይደለም ነው ያሉት። ባሕር ዳር ከተማ በ14 ሳምንት የፕሪሜየር ሊግ ጉዞ 19 ነጥብ ሠብሥቦ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ነጥቡ ከሊጉ መሪ መቻል በ11 ነጥብ ያነሰ ነው።

ዘጋቢ፦ አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here