በታዳጊዎች ስፖርት የምዘና እና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ ተደረገ።

0
6
አዲስ አበባ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕል እና ስፖርት የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ የታዳጊዎችን ዕድሜ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት ማብራሪያ የታዳጊዎችን ዕድሜ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በትክክል ለመከታተል የሕክምና ባለሙያዎችን ያቀፈ ኮሚቴ ከሁለት ወራት በፊት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
ኮሚቴው የራሱን የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ምርመራዎችን የሚያካሂድ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ቀደም ሲል ታዳጊዎች ወደ ውድድር ቦታ ከመጡ በኋላ በሚደረግ ምርመራ ወደ መጡበት የሚመለሱበት አሠራር ለቅሬታ ምክንያት በመኾኑ አሁን ላይ የሕክምና ቡድኑ ክልሎች ባሉበት ቦታ ሄዶ አስቀድሞ እንዲያጣራ ተደርጓል ብለዋል።
በእንደዚህ አይነት ውድድሮች የሚታዩ የዕድሜ ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠር እንዲቻል ታዳጊዎች ከመመዘናቸው በፊት መረጃቸው ወደ ዲጂታል መረጃ ቋት እንዲገባ መደረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በውድድሮች ላይ ሜዳሊያ ከመሠብሠብ ይልቅ በትክክለኛ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችን ማሳተፍ ለስፖርት ዕድገቱ ወሳኝ መኾኑንም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ለዚህም በስፖርት ልማት ላይ የሚሠሩ አካላት እና ክልሎች ኀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይህ አዲስ አሠራር የታዳጊዎችን ትክክለኛ የዕድሜ ልክ ለመለየት እና መረጃዎችን በአግባቡ ለመያዝ እገዛ እንደሚያደርግም ታምኖበታል።
በአዳማ ከተማ አዘጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው የታዳጊወች የምዘና ውድድር ዛሬ የተለያዩ የማጣርያ እና የፍጻሜ ውድድሮች ይደርጉበታል።
ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ኅይለኢየሱስ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here